በኮሮናቫይረስ ከተጠረጠሩ አራት አዲስ ሰዎች አንዱ በአክሱም እንደሚገኝ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም የተባሉ ሌሎች አዲስ አራት ሰዎች መገኘታቸውን አስታወቀ።

የጤና ኢንስቲትዩቱ ይህንን ያሳወቀው በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ሲሆን፤ በቫይረሱ የተጠረጠሩት ሶስቱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ደግሞ ቻይናዊ መሆናቸው ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም አራት ሰዎች በቫይረሱ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ከለይቶ ማቆያ እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል።

በበሽታው ከተጠረጠሩ አንዱ በአክሱም እንደሚገኝ የተቀሩት ደግሞ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ኢንስቲቲዩቱ ያሳወቀ ሲሆን፤ የአራቱም ግለሰቦች ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁ ተነግሯል።

አክሱም ላይ በለይቶ ማቆያ እንዲቆይ የተደረገው ግለሰብ የበሽታው ምልክቶችን በራሱ ላይ በማየቱ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማደረጉን ተከትሎ እንደተለየ ተነግሯል።

ኢንስቲትዩቱ አክሎም እንደገለፀው በቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድ እና እና ሃያ ሰባት የተለያዩ የድንበር መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የማጣራት ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ነው።

ይህ ምርመራ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸውን ተጓዦችን የሚለይ ሲሆን ይሄም የቫይረሱ የበሽታ ምልክት የሚያሳዩትን ለመለየት እንደሚረዳም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

እስከ ጥር 24/2012 ድረስ 47,162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ እንደተደረገላቸው እና ከእነዚህ ውስጥ 1,695ቱ የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሃገር ውሰጥ በሚቆዩበት ወቅት አድራሻቸውን የሚመዘገብ ሲሆን ለአስራ አራት ቀናትም የሚከታተል ቡድን መቋቋሙንም ተገልጿል። በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ታካሚዎችንም ለመውሰድ አራት ተሽከርካሪዎችና ሁለት አምቡላንሶች የተመደቡ መሆኑ ተገልፆ ፤ ለዚሀም የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በቦሌ ጨፌ ያለ የህክምና ቦታ እና የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ለህክምና መስጫነት ተመርጠዋል።