ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የተማሪዎቹ ዕገታ እንደ አገር ከገጠሙን ችግሮች አንዱ ነው" ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን
ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የሚገኙ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ዕገታ በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ካገጠሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ይህንን የተማሪዎች ዕገታ ጉዳይ "በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የተጨበጠ ውጤት ላይ ለማድረስ መንግሥት ሙሉ ኃይሉን አሰባስቦ እየተረባረበ" መሆኑንም አመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሰባት ቤት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በእንጅባራ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት "መንግሥትን በማመን ከወላጆቻቸው ተነጥለው በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ዕገታ በወቅቱ እንደ አገር ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል አንዱ ወቅታዊ ፈተና ነው" ብለዋል።
ተማሪዎቹ ከታገቱበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ መሆኑን የጠቀሱት ም/ጠ/ሚኒስትሩ ተጨባጭ ውጤት ላይ አለመደረሱና የተማሪዎቹ እገታ የወሰደው ረጅም ጊዜ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦችንና ሕዝቡን ባልተቋጨ ጭንቀትና ባልተፈታ ሐዘን ውስጥ እንዲቆዩ አስገድዷቸዋል ብለዋል።
ጨምረውም ችግሩ ውስብስብ መሆኑን አመልክተው በቅርቡ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር ፊት ለፊት በተደረገ ውይይት በተለያዩ ወገኖች ያልተጣሩና ተለዋዋጭ መረጃዎች መሰራጨታቸው የታጋች ቤተሰቦችን ስጋትና ጭንቀት እጅግ መራር እንዳደረገው ለመረዳት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተማሪዎቹና በወላጆቻቸው ላይ ባጋጠመው አሳዛኝ ክስተት እንደወላጅ "ከልባችን አዝነናል" ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
ክስተቱም መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና ችግር ሲያጋጥምም ፈጥኖ የመፍታት አቅሙን ማጠናከር እንዲሁም ድክመቶችን ማረም እንዳለበት በእጅጉ የሚያስገነዝብ ሁኔታ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ዕገታው ያጋጠመበት አካባቢ "የሰላምና የጸጥታ ችግር የሚስተዋልበት በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ የችግሩ ሰለባ ሆነው ቆይተዋል" ሲሉ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የነበረ መሆኑን አመልከተዋል።
በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደተናገሩት በዩኒቨርስቲዎች የተረጋጋ ድባብ እንዳይሰፍን ፍላጎት ባላቸው አካላት ከዚህ በከፋ ደረጃ ጉዳት እንዳይደርስና አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ "በየደረጃው የምንገኝ አካላት በተግባር የመፍትሄው አካል ሆኖ መገኘት የሚጠይቀን ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን" ብለዋል።
ከሰሞኑ ስለታገቱ ተማሪዎች ለመጠየቅ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተካሄዱትን ሰልፎችን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሰልፎቹ በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዳቸው የሚያስመሰግን ነው" ሲሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላትን በተመለከተም "ስህተትን ላለመድገም በማረም፤ እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታ ያለፈቀደውን በግልጽ በማሳወቅ ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆን ኃላፊነትም ግዴታችንም ነው" ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን።