ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ክፍፍልና ጠብ
እኤአ ከ2005 ጀምሮ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለሁለት መከፈሏን ተከትሎ፤ በተለያዩ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና ሌሎች የውጭ አገር ከተሞች የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቷ ምዕመናንም ተከፋፍለው ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
ይህ ግጭት ለበርካታ ጊዜያት በመንግሥት ደጋፊና ተቃዋሚ መካከል እየተካሄደ ያለ ነው ቢባልም፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሁኔታው ከመንግሥት ደጋፊነት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ያስረዳሉ።
በአንድ እምነት ስር በተለያየ መንገድ እየተጓዙ ያሉ ምዕመናን ጠብ እንደሆነም ቢቢሲ ያናገራቸው ምዕመናን ገልፀዋል።
አቡነ አንጠንዮስ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ለጥቂት አመታት ያገለገሉ ሲሆን ከመንበረ ስልጣናቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ሲኖዶሱ ለሁለት ተከፍሏል።
አቡነ አንጠንዮስ ትክክለኛ የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ናቸው ያሉ በአንድ ወገን ተከፍለው፤ ሌሎቹ ደግሞ እሳቸውን በማይቀበሉና በሚያወግዙ መካከል ትገኛለች።
አቡነ አንጠንዮስን የሚደግፈው ጎራ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጳጳስ ይሾምልን ባሉት መሰረት አቡነ መቃርዮስ በስደት ያለውን የኤርትራ ቤተ ክህነትን እንዲያስተዳድሩ ተደርጓል።
ይህ አቡነ አንጠንዮስን ፓትሪያርኩ አድርጎ የሚወስደው አካል 'መናፍቅ'፣ 'ተሃድሶ' የሚል መጠሪያ እንደተሰጠው አገልጋዮቹ ይናገራሉ።
አቡነ አንጠንዮስ ከመንበረ ፖትርያርክነታቸው ከተነሱም በኋላ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ።
ከአስር አመት በላይ ድምጻቸው ሳይሰማ የቆየው አቡነ አንጠንዮስ ባለፈው ዓመት ከቤታቸው ተቀድቶ ነው በተባለ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ፍታሄ ዲሜጥሮስ የተባለ የመንግሥት ልኡክ ቤተክርስቲያኗን ለመምራት እንደመጣና፤ እሳቸውም በምላሹ ጨዋ የሆነ [የቤተክርስቲያን ትምህርት ያልተማረ ] ቤተክርስቲያኗን አያስተዳድራትም ብለው መቃወማቸውን ሲገልፁ ታይቷል።
በዚህ ምክንያት አቡነ አንጠንዮስ የቤተክርስቲያንዋን አሰራር ተከትለው "በምድር የታሰረ በሰማይ የታሰረ ነው . . ." ብለው ገዝተዋል። ግዝቱም እንዲነሳ በሳቸው ወገን ያለው ምዕመናን ለአሰርት ዓመታት ያህል ጠይቀዋል።
በቴልአቪቭ የቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ካህን ሰለሞን ኢዮብ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እርቅና ይቅርታን እንዲወርድ ጥረት እያደረገች ነው ይላሉ።
ካህን ሰለሞን ፓትርያርኩ አቡነ አንጠንዮስ ናቸው ብሎ የሚያምነው ጎራ አካል ሲሆኑ፤ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን አደራ የተሰጣቸው ከመሆናቸው አንፃር ውግዘታቸውን እስኪያነሱ ድረስ ምዕመኑ ከጎናቸው ሊቆም እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
"በሁለቱ ወገኖች መካከል ዕርቅ እንዲወርድ ጥረት አድርገናል፤ ሆኖም ውጤት አልተገኘበትም። አሁን ወደ እግዚአብሄር መጸለይ እንጂ ሌላ ተስፋ የለንም" በማለት ካህን ሰለሞን ያስረዳሉ።
"የቤተክርስቲያናችን ታሪክ እንዲህ አልነበረም፤ ቤተክርስቲያናችን አሳፍረናታል" ይላሉ በለንደን የልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን የአውሮፓ ሃገረስብከት አገልጋይ ቄስ ሺኖዳ እዮብ ሃይለ።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ቴልአቪቭ በሚገኘው የኤርትራ መድሃኒያለም ቤተክርስትያን በካህናትና አገልጋዮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ተዘግቧል።
በወቅቱ በመቋሚያ የተደበደቡ፣ በስለት የተወጉ መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን የእስራኤል ፖሊስም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በእስራኤል ከሚገኙት አራት የኤርትራ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በመድሃኒያለም ቤተክርስቲያን የተፈጠረው ግጭት ከቤተክርስቲያንዋ ውድቀት ጋር የሚያያይዙት ቄስ ሺኖዳ በካህናት፣ ዲያቆናትና መዘምራን የደረሰው ጉዳት "እጅግ የሚያሳዝን ፍጻሜ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
ይህ በተለያዩ የአውሮፓ፣ የሰሜን አሜሪካና እስራኤል ሀገራት ሲታይ የቆየው በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠረው ግጭት መሰረታዊ ምክንያቱ ምንድን ነው? መፍትሄውስ? የሚለው ያነጋገርናቸውን አካላት ያሳሰበ መሆኑን ገልፀዋል።
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መከፋፈል ምክንያት
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፖትርያርክ የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ሙግትና ጠብ ማስከተል ከጀመረ 10 ዓመት ተቆጥሯል።
በተደጋጋሚ በውጭ አገራት በሚገኙ ቤተክርስቲያናት የሚያጋጥም ግጭት ግን 'በመንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች የሚፈጠር ችግር ነው' የሚል ሥም ተሰጥቶት ቆይቷል፤ አሁንም በዚህ መልኩ ይገለጻል።
ይህ መፍትሄ ያላገኘው ሙግት ደግሞ የመከፋፈል ስሜት በመፍጠር የእምነቱን አንድነት እሴቶች የማላላት ብሎም የማጠልሸት ችግሮች እየፈጠረ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ካህናትና ምዕመናን ይናገራሉ።
"በአንድ ፓትሪያርክ፣ በአንድ ጳጳስ እየተመራን በአንድ መንፈስ እንሄድ ነበር። ይህ የከፋፈለን ጉዳይ ግን ከ2005 ጀምሮ [የአውሮጳ አቆጣጠር] የተፈጠረ ነው" ይላሉ በአቡነ መቃርዮስ ስር የሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያን የአውሮጳ፣ አሜሪካና እስራኤል ሃገረስብከት መንበረ ጵጵስና ጸሃፊ ቄስ ገብረሚካኤል ዮሃንስ።
"የኤርትራ መንበረ ፓትሪያርክ ህጋዊ ፓትሪያርኩ አቡነ አንጠንዮስን ማስረጃ ሳያቀርብ ከስልጣናቸው አነሳ፤ አሰሩዋቸውም። የቤተክርስቲያን አባት ያለ ወንጀል መነሳት ስለሌለባቸው በመቃወማችን በቤተክርስቲያንዋ ላይ መከፋፈል ተፈጠረ" ሲሉም ያስረዳሉ።
በ2006 አቡነ አንጠንዮስን የሚቃወሙ ጳጳሳት ወደ ግብፅ በመሄድ ፓትርያርኩ ከመንበራቸው እንዲነሱ የጠየቁ ሲሆን የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጥፋት ያልተገኘበት ፓትሪያርክ ከመንበሩ የማውረድ ስልጣን የላችሁም ብላ መልሳለች። በዚህ ጉዳይም ፍርድ አንሰጣችሁምም ካለቻቸው በኋላ በ2009 ሌላ ፓትሪያርክ መሾማቸውን ቄስ ገብረሚካኤል ይናገራሉ።
የአቡነ አንጠንዮስ እስርና እንግልት የተቃወሙ በውጭ አገር ያሉ የቤተክርስቲያኒትዋ ምዕመናን "ጥያቄያችንም አባታችን ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ነው" ይላሉ ቄስ ገብረሚካኤል።
ቄስ ሽኖዳ "ይህች ቤተክርስቲያን እንደ ሽንኩርት እየተላጠች ነው። ይቅርታን በማይሰብኩ ሰዎች ደግሞ እንደ 'ሕልበት' እየተመታች ነው። ከኢትዮጵያ ይሁን ከሌሎች ቤተክርስቲያናት ትምህርት ወስደን ወደ አንድነት መምጣት አለብን" በማለት አሁን ያለውን መከፋፈል ያወግዛሉ።
ቤተክርስቲያን ሰላምና ፍቅርን ማስተማርና በተግባር ማሳየት ነበረባት የሚሉት ቄስ ሰለሞን "አሁን ቤተክርስቲያናችን የሚያሳዝን መገዳደል የሚፈጸምባት ሆናለች፤ ይህም ሁሉንም አሳዝኗል" ብለዋል።
የዚህ ችግር ምክንያት በኤርትራ ያለው ሲኖዶስ አቡነ አንጠንዮስን በሚመለከት የእርቅ ሀሳብ ይዞ ከመጣ በኋላ ተመልሶ ሲተወው የተፈጠረው መከፋፈል እንዳገረሸ በመግለጽ ችግሩ ለአመታት ሲንከባለል የቆየ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
"ይህን ለዚህ ሁሉ ሊያደርሰን አይገባም ነበር" ያሉት ቄስ ሰለሞን በእስራኤል ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በሦስት እንደተከፈሉ ይናገራሉ።
የመንግስት ደጋፊ ነው ተብሎ የሚነገርለት አንደኛው የቤተክርስቲያኒቱ አካል በቅርቡ ወደ አሜሪካ ባደረገው ጉዞ ወቅት "አቡነ አንጠንዮስ እስረኛ ያደረጉት ራሳቸው እንጂ የኤርትራ መንግሥት እጁ የለበትም፣ አላሰራቸውም" በማለት ለቪኦኤ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ቢቢሲ ቴልአቪቭ ከሚገኘው የዚህ ወገን ሃገረስብከትም ሆነ ከኤርትራ ቤተክህነት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
እርቅ ታስቦ ያውቃል?
ፓትሪያርክ የምትሾምና የምተቀባው የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከኤርትራ ጋር ባላት ታሪካዊ ዝምድና ምክንያት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግዋንም ካህናቱ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ይላሉ ቄስ ሰለሞን "በኛ እምነት የቤተክርስቲያንዋ ስልጣን ከእጇ ወጥቶ ወደ ሌላ አካል ስለሄደ እርቁ ሊሳካ አልቻለም። ስልጣንዋ በቤተክርስቲያኗ ስር ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ባልተጨካከንን ነበር። ግን ወደ አንድ አካል እንድንመጣ አይፈለግም። "
መጀመሪያ ላይ በብዙ መንገድ ይህ ችግር ለመፍታት ተሞክሮ ነበር የሚሉት ቄስ ገብረሚካኤል፣ በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ አምባሳደርና አሁን በህይወት የሌሉት ግርማ አስመሮም ጉዳዩ ሲጀመር ከስር መሰረቱ መፈታት እንዳለበትና ወደ እርቅ እንዲመጡ ጥረት ማድረጋቸውን ያወሳሉ።
"በኛ በኩል ፈቃደኞች ብንሆንም፤ አስመራ ግን ማንኛውም አይነት ግንኙነት እንዳይኖር ተከልክሏል የሚል ወሬ እንደተሰማ ተቋረጠ" በማለት ቄስ ሰለሞን ያስረዳሉ።
"ከዚህ በኋላም ምእመኑ ቢንቀሳቀስም አሁንም በአስመራ በኩል ፈቃድ አልተገኘም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክፍፍሉ ጉዳት
ይህ ሁሉ ችግር የቤተክርስቲያንዋ '"ውድቀት" ማሳያ ነው ያሉት ቄስ ሺኖዳ "ውድቀቱ የሚገባን ለይቅርታና አንድነት ዝግጁ ስንሆን ነው" ብለዋል።
"ኤርትራ ባለው 'ምስለ ሲኖዶስ' የሚተዳደሩ ቤተክርስቲያናት አስር አመት ሙሉ ስም ማጥፋት ላይ ነው ያሳለፉት። 'መናፍቃን ገብተዋል፣ እነዚህ ከሲአይኤ ጋር ግንኙነት ያላቸው' እየተባለ ስጋትና ፍርሃት ሲሰበክ ኖሯል። በዚህ ፈንታ ይቅርታን አላስተማሩም። ለዚህ ነው ሰው ቤተክርስቲያን ውስጥ እየተጣላ ያለው" ይላሉ።
ሌላው የቤተክርስቲያንዋ ትልቁ ችግር አገልጋዩ እንደሆነ የሚናገሩት ቄስ ሺኖዳ "በስሜት የሚነዳ፣ ፈሪሃ እንግዚአብሄር የሌለው አገልጋይ ነው ያላት። ከስጋዊ አስተሳሰብ ወጥተን ለመነጋገር የኔ ወገን መሰማት አለበት የሚለው ንትርካችን መቆም አለበት" ይላሉ።
እስከ አሁን እየቀጠለ ባለው የቤተክርስቲያን ግጭት ግን በስደተኛው ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ በመዝለቅ ችግሩ የከፋ እንዲሆን እያደረገው ነው ይላሉ ካህናቱ።
"ተጽእኖው ይህ ነው ብሎ መግለጽ አይቻልም" የሚሉት ቄስ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም "ቤተክርስቲያንዋ ላይ በፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ችግሩን አባብሶታል" ሲሉ ያስረዳሉ።
"የቤተክርስቲያኒቱ ችግር ፖለቲካ ነው። በአገራችን የሃይማኖት ነጻነት ቢኖር ኖሮ ፓትሪያርኩ ስለ ተከሰሱበት ወንጀል እዛው ሆነን እንታገል ነበር። ግን በዚህ ምክንያት ተሰደናል፤ ተሰደን በምንኖርበት አገር ደግሞ ይህ እየተፈጠረ ያለው ችግር ተጽእኖ እያሳደረብን ይገኛል" ይላሉ።
ቄስ ሰለሞን ችግሮቹ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እሴቶችን እየሸረሸሩ ስለ መሆናቸውም ያስረዳሉ።
"ፓትሪያርኩ ላይ የተፈጠረው የህግ ጥሰት የእምነታችን አምድ የሆነውን ፍቅር ሸርሽሮታል። የአምልኮ ሥፍራዎች እንደ መጠጥ ቤቶች ሆነዋል። እርስ በእርሳችን እየተጣላን ምእመኑ እንዲጠፋ ቤተክርስቲያን ባዶዋን እንድትቀር ራሳችን ጠላቶች ሆነንባታል" ሲሉ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።