በቃፍታ-ሸራሮ ብሔራዊ ፓርክ በተከሰተው ሰደድ እሳት 1,500 ሄክታር ደን ወደመ

በሰሜን ኢትዮጵያ በቃፍታ-ሸራሮ ብሔራዊ ፓርክ በተከሰተው ሰደድ እሳት ሳቢያ 1,500 ሄክታር ደን መቃጠሉ ተገለጸ።

የቃፍታ-ሸራሮ ብሔራዊ ፓርክ አስተባባሪ አቶ ዘነበ አረፋይኔ ለቢቢሲ እንደገለፁት፤ ሰደድ እሳቱ የተነሳው ፓርኩ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ገብተው ወርቅ ለማውጣት የሚሞክሩ እረኞች ባቀጣጠሉት እሳት እንደሆነ ታውቋል።

አስተባባሪው "እሳቱ በተለይም በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖችን እንዳያባርር ተሰግቷል" ብለዋል።

ሰደድ እሳቱ ሰኞ አመሻሽ ላይ እንደተከሰተና ዛሬ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ አቶ ዘነበ ገልጸዋል።

ሰደድ እሳቱ እንደተነሳ ለዱር እንስሳትና ደን ጥበቃ ባለስልጣን እንዳሳወቁ የተናገሩት አስተባባሪው፤ እሳቱን ለማጥፋት የትግራይ ምዕራባዊ ዞንና የቃፍታ ሑመራ ወረዳ መስተዳድር የአደባይ ሕዝብ መተባበሩን አስረድተዋል።

ማኅበረሰቡ ሰደድ እሳቱን በባህላዊ መንገድ ለማጥፋት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ዛሬ ጠዋት እሳቱን መቆጣጠር መቻሉንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአከባቢው የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የትግራይ ልዩ ኃይል ፖሊሶች እሳቱን በማጥፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውም ታውቋል።

አስተባባሪው ዳግመኛ ሰደድ እሳት እንዳይከሰት ከፍትኛ ክትትልና ጥንቃቄ መወሰድ አለበት ብለዋል።