ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የግብጽዊው አርቲስት ድርጊት አውሮፕላን አብራሪው እስከወዲያኛው ከሥራቸው እንዲባረሩ አደረገ
ግብጻዊው ተዋናይና ድምጻዊ ከሥራ አጋሮቹ ጋር በመሆን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየበረረ በነበረበት ወቅት ድንገት ብድግ ብሎ ወደ አብራሪዎቹ ክፍል ያመራል።
ይህ ዝነኛ ተዋናይ በረዳት አብራሪው ቦታ ተቀምጦ አውሮፕላኑን ሲያበር የተቀረፀ ሲሆን ይህ እንዲሆን የፈቀዱት የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ አውሮፕላን እንዳያበሩ በግብጽ መንግሥት ታግደዋል።
ስመ ጥሩ ተዋናይ መሐመድ ረመዳን የተባለ ሲሆን በግል አውሮፕላን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየሄደ ባለበት ወቅት ነው አብራሪው ከጎናቸው አስቀምጠውት የታየው።
ዝነኛው ተዋናይና ድምጻዊም በረዳት አብራሪው ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስልን በሞባይል ቀርጾ በቲውተር ገፁ ላይ የለጠፈ ሲሆን መቆጣጠሪያውን ሲይዝም ይታያል።
ረዳት አብራሪውም በዚሁ የተነሳ ለዓመት ያህል አውሮፕላን በደረሰበት እንዳትደርስ በማለት ታግዷል።
የመሐመድ ድርጊት መዘዙ በረራውን ያካሄደው የስማርት አቪየሽን ባለሰልጣናትንም ጋር ደርሷል፤ ከስልጣናቸው እንዲለቁ መደረጉ ተገልጿል።
የግብጽ ሲቪል አቪየሽን ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ "የግብጽን ሲቪል አቪየሽን ህግ መጣሳቸው እንደተረጋገጠ አብራሪው ለግዴለሽነቱና ኃላፊነት ለጎደለው ድርጊቱ እንዲሁም ሌሎች አካላት ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደናል" ብሏል።
ሚኒስቴሩ አክሎም የአቪየሽን ደህንነት ለግብፅ አየር መንገዶች በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብሏል።
መሐመድ ረመዳን ከ7 ሚሊዮን በላይ የዩቲዩብ ተከታዮች ያሉት ሲሆን ይህንን ምስል በቲውተር ገፁ ላይ የለጠፈው የዛሬ ሳምንት ገደማ ነበር።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይም "ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላን ላበር ነው" ሲል ይደመጣል።
በምስሉ ላይ ወደ አብራሪዎቹ ክፍል ሲገባ ያለው ክፍል ተቆረጦ ያጠረ ሲሆን የረዳት አብራሪው መቀመጫ ላይ ሲቀመጥና መቆጣጠሪያውን ሲይዝ ግን ይታያል።
ማንነቱ ያልታወቀ ሌላ ሰው "ፈጣሪ ምስክሬ ነው መሐመድ ረመዳን በአሁን ሰዓት አውሮፕላን እያበረረ ነው" ሲል ይደመጣል።
የግብጽ አቪየሽን ባለስልጣን መንገደኞች አውሮፕላኑ በበረራ ላይ እያለ ወደ አብራሪው ክፍል እንዳይገቡ የሚከለክል ህግ አለው።
አንዳንዶች በተዋናዩ የተበሳጩ ሲሆን የእርሱን ሥራዎች ማየት ማቆም አለብን ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡም አሉ።
ረመዳን በግብጽ ሲኒማዎችና ድራማዎች ላይ በብዛት የሰራ ሲሆን ወደ ሳዑዲ የሄደውም የባንድ አባላቱን ይዞ በአንድ ፌስቲቫል ላይ ለመዝፈን እንደሆነ ገልጿል።
የ31 ዓመቱ ተዋናይ በዩቲዩብ ላይ 158 ሚሊዮን ጊዜ የታየለት ሙዚቃ አለው።
ይህ ተዋናይና ድምፃዊ ዝናው ጣሪያ የነካ ቢሆንም አከራካሪ ጉዳዮችም አያጡትም።
ከዚህ ቀደም በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ አካሉን የሚያጋልጥ አለባበስ ለብሶ ሲደንስ ታይቶ በአድናቂዎቹ መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶ ነበር።
ከሦስት ዓመታት በፊት ደግሞ ስለገዛቸው ሁለት ቅንጡ መኪኖች ጉራውን በመቸርቸሩ 'ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አድናቂዎቹ ስሜት አይጨነቅም' በሚል ወቀሳ ቀርቦበት ነበር።