በአውስትራሊያ የውድድር ፈረሶች እየታረዱ ነው በሚል የቀረበው ውንጀላ ላይ ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, ABC 7.30
በአውስትራሊያዋ ኩዊንስላንድ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የእርድ አገልግሎት መስጫ- ቄራ ውስጥ ፈረሶች ሲጉላሉና ሲጎሳቆሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በኤቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከተላለፈ በኋላ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
በቴሌቪዥን ጣቢያ የተሰራ ዘገባ እንደሚያሳየው ከግልቢያ ውድድር የሚገለሉ ፈረሶች እየታረዱ መሆናቸውን ነው።
በአውስትራሊያ ፈረሶችን ማረድ ሕጋዊ ቢሆንም በአንዳንድ ግዛቶች ግን ከውድድር በጡረታ የተገለለ ፈረሶች ወደ ሌላ የእንስሳት ማቆያ እንዲዛወሩ ብቻ ይፈቅዳሉ።
በአውስትራሊያ የፈረስ ግልቢያ ተወዳጅ ስፖርት ሲሆን ከፍተኛ ገንዘብም ይገኝበታል።
ባለስልጣናት በቅርቡ ከሚካሄደው የፈረስ ግልቢያ ውድድር አስቀድሞ የቀረበውን ይህንን ውንጀላ አስመልክተው በሰጡት ምላሽ "አስደንጋጭ" ብለውታል።
"እንስሳትን ማጎሳቆልና ማንገላታት አስነዋሪ ተግባር ነው" ያሉት የኪዊንስላንድ የግልቢያ ውድድር ሚኒስትር ስተርሊንግ ሂንቺልፍ ናቸው።
የአካባቢው አስተዳደር በኤቢሲ ዘገባ ላይ ወደ ተጠቀሰው የእርድ አገልግሎት መስጫ ባለሙያዎችን ወዲያውኑ መላካቸውን አስታውቀዋል።
የእርድ አገልግሎት በሚሰጠው በዚህ ቄራ ውስጥ በ22 ቀን ብቻ 300 የውድድር ፈረሶች መታረዳቸው በቴሌቪዥን ጣቢያው ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።
ዘገባው አክሎም ፈረሶች በዚህ ቄራ ውስጥ ይመታሉ፤ ይንገላታሉ ሲል ይጠቅሳል።
የአውስትራሊያ የፈረስ ግልቢያን የሚያስተዳድረው አካል ፈረሶች ጡረታ ወጥተው ከውድድር ከራቁ በኋላ እምጥ ይግቡ ስምጥ ማወቅ አልቻልኩም ሲል ተናግሮ ነበር። ይህንን መዝግቦ በመያዝ የሚከታተል አካል በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲቋቋምም ሃሳብ አቅርቦ ነበር።
የፈረስ ግልቢያ ውድድር የሚያካሂደው አካል በእንስሳት መብት ተሟጋቾች ለዓመታት ይብጠለጠል ነበር።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቅርቡ የሚካሄደውን የፈረስ ግልቢየያ ውድድር ይታደሙታል ተብሎ ይጠበቃል።
















