ሜክሲኮ ውስጥ የኤል ቻፖን ልጅ ለመያዝ ከባድ ውጊያ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Image copyrightAFP/GETTY IMAGES
በሰሜናዊ ሜክሲኮ አደገኛ የሚባለው የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ያለበት ስፍራ ከታወቀ በኋላ በጸጥታ ኃይሎችና በቡድኑ አባላት መካካል ከባድ ውጊያ መካሄዱ ተነገረ።
ሲናሎዋ የተባለው የዚህ ቡድን መሪ ኦቪዲዮ ጉዝማን ሎፔዝ ያለበት ቦታ ሊደረስበት የቻለው ፖሊስ በሚያደርገው መደበኛ አሰሳ ወቅት ነበር።
ኦቪዲዮ አሜሪካ ውስጥ የዕድሜ ልክና የ30 ዓመታት እስር የተፈረደበት የታዋቂው ዕፅ አዘዋዋሪ ዮአኪን ጉዝማን ወይም ኤል ቻፖ ልጅ ነው ተብሏል።
የ62 ዓመቱ ኤል ቻፖ ኒው ዮርክ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርቦ ዕፅ ማዘዋወርና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ በ10 ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ እስር ተፈረዶበታል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኤል ቻፖ ከአራት ዓመታት በፊት ከሜክሲኮ እስር ቤት ከምድር በታች በተቆፈረ መተላለፊያ አምልጦ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ተይዞ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጥቷል።
ኤል ቻፖ አሁን ልጁ ይመራዋል የሚባለውና የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደሚሉት ወደ አገራቸው ከሚገባው ዕፅ ውስጥ ከፍተኛውን መጠን የሚያቀርበው ሲናሎዋ የተባለው ቡድን መሪ ነበር።
በሰሜናዊ ሜክሲኮ የሚገኘው የኩሊያቻን ግዛት ባላስልጣናት እንዳሉት ፖሊሶች አሰሳ በሚያደርጉበት ጊዜ ኦቪዲዮ ጉዝማን ያለበት ቤትን ካገኙ በኋላ የዕፅ አዘዋዋሪው ቡድን አባላት መሪያቸውን ለማስመለጥ ከባድ ጥቃት ሰንዝረዋል።
የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኑ መሪ ኦቪዲዮ ጉዝማን በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከአባቱ እስር በኋላ የሲናሎዋ ቡድንን በመምራት ቁልፍ ሚና እንዳለው ይነገራል።
የሜክሲኮ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ኦቪዲዮ ከዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ በቀረቡበት በርካታ ክሶች አሜሪካ ውስጥ በህግ ይፈለጋል። ቀደም ሲልም ለአጭር ጊዜ በፖሊስ ተይዞ መለቀቁም ተዘግቧል።
በፖሊሶችና በዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኑ አባላት በተካሄደው ከባድ ውጊያ ሳቢያ ስለደረሰው ጉዳት ከባለስልጣናት የወጣ ምንም መረጃ ባይኖርም፤ ከከተማዋ እየወጡ ያሉ ምስሎች በመንገዶች ላይ የወደቁ አስከሬኖችን ያሳያሉ።












