ካሊፎርኒያ ከእንስሳት ፀጉር የሚሰሩ ምርቶችን በማገድ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ግዛት ሆነች

ካሊፎርኒያ፤ ከእንስሳት ፀጉር የሚሠሩ ምርቶች እንዳይመረቱና እንዳይሸጡ በማገድ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ግዛት ሆነች።
በመሆኑም የግዛቷ ነዋሪዎች ከ2023 ጀምሮ ከእንስሳት ፀጉር የተሠሩ ምርቶችን መሸጥም ሆነ አልባሳት፣ ጫማ፣ ቦርሳዎችን መሥራት አይችሉም።
ውሳኔው እገዳው እንዲጣል ለተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩትን የእንስሳት መብት ተሟጋቾች አስደስቷል።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ጌቪን ኒውሰም፤ ከድመት፣ ከውሻና ከፈረስ በስተቀር ሌሎችን እንስሳት በሰርከስ ትዕይንት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚከለክለውን ረቂቅ ሕግም ፈርመዋል።
ነገር ግን ሕጉ በሰሜን አሜሪካ የሚዘወተረውን የኮርማ እና የፈረስ ግልቢያ ስፖርት ላይ ተግባራዊ አይሆንም።
"በእንስሳት ደህንነት ጥበቃ ዙሪያ ካሊፎርኒያ መሪ ናት፤ ዛሬ ደግሞ አስተዳዳሩ ከእንስሳት ፀጉር የተሠሩ ምርቶችን እንዳይሸጥ ለማድረግ ሕግ አውጥቷል" ሲሉ አስተዳዳሪው ጋቪን በመግለጫቸው ተናግረዋል።
እገዳው ግን በቆዳ ምርቶች ላይ ማለትም በላም፣ በአጋዘን፣ በበግና በፍየል ቆዳ ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆን የሳንፍራንሲስኮ ክሮኒቸል ዘግቧል።
ከዚህም በተጨማሪ በእንስሳት አምሳያ ከእንስሳት ምርቶች የሚሠሩ አሻንጉሊቶች ላይ ተግባራዊ እንደማይሆንም ተነግሯል።
ይህንን ሕግ ጥሶ የተገኘም እስከ 500 ዶላር ቅጣት፤ ሕጉን በተደጋጋሚ ለጣሰም እስከ 1000 ዶላር ያስቀጣል።
የአሜሪካ ሁዩማን ሶሳይቲ አሜሪካ የግዛቷን አስተዳደር እና ሕግ አውጪዎቹን እንዲሁም የካሊፎርኒያ ዜጎች ገበያቸው በእንስሳት ፀጉር የተሠሩ ምርቶች ፍላጎቶችን እንዲያስተናግዱ ባለመፍቀዳቸው አድናቆቱን ችሯል።
ይሁን እንጂ ውሳኔው የእንስሳት ተዋፅኦ የማይጠቀሙትን አክራሪ ቬጋኖች (እንስሳትንም ሆነ የእንስሳት ተዋፅኦ የማይጠቀሙ) አጀንዳ ለማስተናገድ ከፀጉር የሚሠሩ ምርቶችን በመከልከል፤ በምንለብሰውና በምንመገበው ላይ እገዳ ለመጣል አንድ እርምጃ ነው ሲል ፈር ኢንፎርሜሽን ካውንስል ተችቶታል።
ባሳለፍነው ግንቦት ወር አንድ በፋሽን የተሠማራ ድርጅት እስከ 2020 ድረስ የእንስሳትን ፀጉር መጠቀም እንደሚያቆም አስታውቆ ነበር።
በየካቲት ወርም እንዲሁ የእንግሊዙ ሰልፍሪጅስ ከየካቲት 2020 ጀምሮ የእንስሳት ቆዳ ውጤቶችን መሸጥ ሊያግድ እንደሚችል ማስታወቁ ይታወሳል።














