ናይጄሪያ፡ 500 የሚጠጉ ወንዶች ታጉረውበት ከነበረው ህንጻ ነፃ ወጡ

በሰሜን ናይጄሪያ በምትገኘው ካዱና ከተማ ውስጥ ታሥረው ወሲባዊ ጥቃት እና እንግልት ሲደርስባቸው ነበር የተባሉ 500 የሚደርሱ ወንዶች ነጻ መውጣታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

አምስት ዓመት ከሚሆናቸው ህጻናት አንስቶ እስከ ጎልማሶች ድረስ በአንድ ህንጻ ውስጥ ታጉረው ነበር። ህንጻው የእስልምና ትምህርት መስጫ ነው የሚል ሽፋን ተሰጥቶት ነበር ተብሏል።

የካዱና ከተማ ፖሊስ ኃላፊ አሊ ጃንጋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ስለ ህንጻው ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ወንዶቹን ነፃ ማውጣት ችለዋል። አንዳንዶቹ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው፣ የተቀሩት ደግሞ በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ተዳክመው ነበር።

"ህንጻው ሰዎች የሚሰቃዩበት፣ የባርነት ቤት ነበር" ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል። በህንጻው ውስጥ ታግተው የነበሩት ወንዶች ለዓመታት ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸው፣ ምግብም ይከለከሉ እንደነበረም ገልጸዋል።

መምህራን ናቸው የተባሉ ስምንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ከታጋቾቹ አንዱ የሆነው ቤል ሀምዛ "በዚህ ህንጻ ውስጥ ለሦስት ወር እግሬን ታሥሬ ቆይቻለሁ፤ የእስልምና ትምህርት ቤት ነው ይላሉ፤ ነገር ግን ከህንጻው ለመውጣት የሚሞክር ሰው ጣሪያ ላይ ተሰቅሎ ከባድ ቅጣት ይቀጣል" ብሏል።

አንዳንዶቹ ታዳጊዎች ለፖሊስ እንደተናገሩት፤ ቤተሰቦቻቸው ወደ ህንጻው የወሰዷቸው የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት ቦታ ነው ብለው በማመን ነበር።

ከታዳጊዎቹ ሁለቱ የተላኩት ከቡርኪና ፋሶ ሲሆን፤ የተቀሩት የሰሜን ናይጄሪያ ተወላጆች ናቸው።

በአካባቢው የእስልምና ትምህርት ከሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች በጥቂቱ ውስጥ ታዳጊዎች እንደሚበዘበዙ፣ እንዲለምኑ እንደሚገደዱም ይነገራል።

አንድ ወላጅ "ልጆቻችን እንዲህ ያለ ስቃይ እንደሚደርስባቸው አናውቅም ነበር" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ነፃ የወጡት ወንዶች በጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የከተማዋ ባለሥልጣኖች ለቢቢሲ ገልጸዋል።