ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መሐመድ አሊ፡ የአልሲሲን ገመና አደባባይ ያሰጣው ግብጻዊ
የግብጽ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንዳወጡት መረጃ ከሆነ በዚያች አገር በቅርቡ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ቢያንስ አንድ ሺ ዜጎች ተለቅመው ታስረዋል። በክንደ ብርቱው አብዱልፈታህ አልሲሲ ላይ በዚህ ፍጥነት ተቃውሞ ይነሳል ያለ ማንም አልነበረም።
ውስጥ ውስጡን ኑሮ አልገፋ ያላቸው ግብጻዊያን በመንግሥት ላይ እያጉረመረሙ ቢቆዩም ሕዝብን አደባባይ ያስወጣው ግን በዋናነት የመሐመድ አሊ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።
መሐመድ አሊ እንደሚለው አብዛኛው ግብጻዊ በችጋር ተጠፍንጎ ሳለ አብዱልፈታህ አልሲሲ ግን ለሚስታቸው እና ለጄኔራሎቻቸው እጅግ ቅንጡ ቪላ ቤቶችን እያስገነቡ ያንበሸብሻሉ።
አልሲሲ ግን ይህንን ክስ አይቀበሉትም። "ቅጥፈት ነው፤ እንዲህ የሚያስወሩት የኢስላም አክራሪዎች ናቸው" ብለዋል፤ ከሰሞኑ ኒውዮርክ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጎን ቁጭ ብለው ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር መግለጫ።
ያልተጠበቀውን የአደባባይ ተቃውሞ ማን ጠራው?
ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ግብጻዊያን ታሪካዊው ታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ ሲወጡ ዓለም ተደምሟል። ምክንያቱም በዚያች አገር የአልሲሲ ጦርና አስተዳደር ተቃውሞ በጭራሽ እንዳይነሳ፤ እንዲያውም ጭራሽ እንዳይታሰብ አድርገዋል ተብሎ በመታመኑ ነው።
በተለይ በዲሞክራሲ ለመመረጥ የመጀመሪያ የሆኑት መሐመድ ሙርሲ ፍርድ ቤት ሳሉ እምብዛም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት መሞታቸው ከተገለጸ በኋላ በዚያች አገር ተቃውሞ መቆስቆስ የሚመከር ሆኖ አልታሰበም።
ዓለም በአልሲሲ ላይ ሆ ብሎ የሚነሳ ተቃዋሚም ሆነ ተቃውሞ ከእንግዲህ እንደማይኖር በደመደመበት ወቅት ግን አንድ የ45 ዓመት ጎልማሳ እመኑኝ ሕዝብ በቅርቡ አደባባይ ይወጣል ሲል ተነበየ። እንዳለውም ሆነ። ለዚህ ተቃውሞ መነሻ የሆነውም ይኸው ጎልማሳ ነው፤ መሐመድ አሊ።
መሐመድ አሊ የቢዝነስ ሰው ነው። ለጊዜው ስፔን አገር ነው የሚኖረው። ለቤተ መንግሥቱ ቅርብ ነበር። ከመስከረም ጀምሮ ታዲያ አልሲሲ ምሥጢሬ ብለው የያዙትን ሁሉ አውጥቶ ይዘከዝክ ጀመር። በቪዲዮ ለሚሊዮኖች አዳረሰው፤ ካለፈው መስከረም የጀመረ ዛሬም አላቆመም።
መሐመድ ቢያንስ በቀን አንድ ቪዲዮ ለሕዝብ ሳያደርስ አይውልም። ታዲያ በየጊዜው የሚያቀብለው መረጃ ግብጻዊያንን ጉድ የሚያሰኝ ነበር።
በዋናነት ታዲያ የአብዱልፈታህ አልሲሲን ንቅዘት፣ የወታደሩን በሙስና እስካፍንጫ መዘፈቅ በማስረጃ እያስደገፈ ነበር የሚያቀርበው፤ ማስረጃው የቃል ቢሆንም።
የመሐመድ አሊ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች
"ካሜራ ፊት ቁጭ ብሎ በቀላል መንገድ ነው ቪዲዮዎችን የሚለቃቸው፤ አንዳንድ ጊዜ ንዴቱንና መንገብገቡን ፊቱ ላይ ትመለከተዋለህ" ይላል የቢበሲ አረብኛ ባልደረባ የሆነው መሐመድ ያህያ።
መሐመድ አሊ ይፈጽማሉ ለሚላቸው ንቅዘቶች የጽሑፍ መረጃ አያቀርብም፤ ነገር ግን የተሳተፈባቸውን ፕሮጀክቶች ዘክዝኮ ያስቀምጣል። የአልሲሲ ደጋፊዎች የሚናገረውን በጥርጣሬ ቢመለከቱትም ተቃዋሚዎች ግን እምነት ይጥሉበታል። ያ ነው ግብጻዊያኑን አደባባይ ያስወጣቸው።
ምንም እንኳ የግብጽ ሚዲያ አንድም ቀን የርሱን ቪዲዮዎች አሳይቶ ባያውቅም እርሱ ግን ቤቱ ቁጭ ብሎ ሚሊዮኖች በቀላሉ መድረስ ችሏል።
የመሐመድ አሊ ቪዲዮዎች እጅግ ገናና ከመሆናቸው የተነሳ አልሲሲ እሱ ለሚያነሳቸው ክሶች ስሙን ሳይጠቅሱም ቢሆን ምላሽ ለመስጠት ተገደው ነበር።
መሐመድ አሊ የአልሲሲን ምላሽ ከሰማ በኋላ እንዲያውም ባሰበት። ዙፋናቸውን በአጭር ጊዜ መንግሎ እንደሚነቅለው መዛት ጀመረ።
መሐመድ አሊ ማን ነው?
መሐመድ አሊ ኮንትራክተር ነው። "አምላክ" የሚባል የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት ነበረው። ለግብጽ መከላከያ በርካታ የግንባታ ሥራዎችን ተኮናትሮ እንደሰራ ይነገራል።
መሐመድ አሊ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ተዋናይ ነበር። "ዘ አዘር ላንድ" በሚል ፊልም መሪ ገጸ ባሕሪን ተላብሶ ተውኗል። በተዋናይነቱ ግን ያን ያህልም ገናና አልነበረም።
መሐመድ ድንገት ድርጅቱን ዘግቶ፤፤ ማቄን ጨርቄን ሳይል ስፔን ገባ።
ወዲያውኑ የወታደሩንና የአልሲሲን ገመና የያዙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን መልቀቅ ጀመረ።
የመሐድ አባት አቶ አሊ አብዱል ካሊክ እውቅ የክብደት ማንሳት ስፖርተኛ ነበሩ። በኋላ ላይ ነው ወደ ተቋራጭነት ጠቅልለው የገቡት። ይህንን ሥራቸውን ልጃቸው ወረሰው።
መሐመድ በግብጻዊያን ዘንድ እሳት ከለኮሰ በኋላ አባቱ ለመንግሥት ቅርብ በሆነው የአገሬው ቲቪ ቀርበው ነበር። ልጃቸውን አውግዘዋል። "ልጄ አይደለህም" ብለውታል።
"ልጄ የሚያወራውን አትስሙት፤ ሙልጭ ያለ ውሸት ነው" ብለዋል። ለኛ ማደግና መለወጥ የወታደሩ ውለታ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
"ሠራዊቱ ገንዘቤን በላኝ"
መሐመድ አሊ "ከሠራዊቱ ጋር የተያያዙ ግንባታዎችን ስሠራ ብቆይም..." ይላል "...ገንዘቤን ግን ሊከፍሉኝ አልቻሉም።"
በሚሊዮን የሚቆጠር የግብጽ ፓውንድ ጥዬ ነው የወጣሁት ይላል። ከአገር የወጣውም የሚደርስበትን በመፍራት እንደሆነም ይናገራል።
በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስቻለው ከሠራዊቱ ጋር የነበረው የሥራ ውል እንደሆነ ይነገራል። ይህ እውነታ ውስጥ አዋቂ ስለመሆኑም ጥርጣሬ እንዳይኖር አስችሏል።
አልሲሲና የቅርብ ጄኔራሎች ስለሚያስገነቧቸው ቪላዎች ቅንጡነት፣ ስለሚወጣባቸው ወጪ፣ በድሀው ገንዘብ ጥቂት ጄኔራሎች እንዴት እንደሚራጩበት በዝርዝር ይናገራል።
ይህንን ቪዲዮ ከለቀቀ በኋላ የግብጽ አቃቢ ሕግ ሙሐመድ አሊን "አገር በመክዳት" ከባድ ወንጀል ከሶታል፤ በሌለበት።
ግብጻዊያን መሐመድን ለምን ሰሙት?
በቅርብ በወጣ መረጃ 32.5% ግብጻዊያን በድህነት አዘቅት ውስጥ ናቸው። ይህ አሐዝ በ2015 እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ 27.8% ብቻ ነበር።
የድህነቱ መበራከት ግብጻዊያኑ አደባባይ እንዲወጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።
ሆኖም ግን የዓረቡ አብዮት እንዳይሆኑት ከሆነ በኋላ በአብዛኛው ዜጋ ዘንድ ለተቃውሞ የመታከት ዝንባሌ ይታያል። በዚህ ላይ የአልሲሲ ክንደ ብርቱነት ተቃውሞው ብዙም ፈቀቅ እንዳይል ሳያደርገው አልቀረም።
ያም ሆኖ የባለፈው ሳምንት በበርካታ ከተሞች ሕዝብ አደባባይ መውጣቱ የብዙዎችን ግምት የተሳሳተ አድርጎታል።
አልሲሲ በቅርቡ ወጣቶችን ሰብስበው እንደተናገሩት ቤተ መንግሥት እየገነቡ እንደሆነ ባይክዱም ግንባታው ለግብጻዊያን እንጂ ለሌላ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ከአልሲሲ የመጣው የግንባታ ማረጋገጫ ታዲያ የመሐመድ አሊ ክሶች እንዲሁ ተራ አሉባልታዎች እንዳልነበሩ ማረጋገጫ የሰጠ ሆኗል።