ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ መተግበሪያዎችን አገደ
ፌስቡክ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ መተግበሪያዎችን ማገዱን ይፋ አደረገ። የካምብሪጅ አናሊቲካ የመረጃ ምዝበራ ቅሌትን ተከትሎ ፌስቡክ ባደረገው ምርመራ መተግበሪያዎቹን እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2018 ላይ ካምብሪጅ አናላቲካ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ መመዝበሩን ተከትሎ፤ ፌስቡክ ከፍተኛ ወቀሳ ተሰንዝሮበታል። ካምብሪጅ አናሊቲካ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ ሰብስቦ ፖለቲካ ነክ ማስታወቂያዎችን ለማሰራጨት እንደተጠቀመበት መነገሩም ይታወሳል።
ፌስቡክ በወቅቱ አምስት ቢልየን ዶላር የተቀጣ ሲሆን፤ የሰዎችን ግላዊ መረጃ ከመመዝበር ጋር በተያያዘ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ የተቀጣ ድርጅት አልነበረም።
ፌስቡክ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትችቱ እየበዛበት ሲመጣ፤ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ አሠራሮችን መተግበር ጀምሯል። ፌስቡክ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጠበቃዎችን፣ ኢንጂነሮችን እና የመረጃ ጥበቃ ተመራማሪዎችን አሰማርቶ መተግበሪያዎቹ ላይ ምርመራ ማድረግ የጀመረውም ለዚህ ነው።
ፌስቡክ ስላገዳቸው መተግበሪያዎች ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
አብዛኞቹ መተግበሪያዎች ቢታገዱም፤ ተጠቃሚዎች ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ እንዳልነበረ ድርጅቱ ገልጿል።
ከመተግበሪያዎቹ መካከል የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ ከገጻቸው ላይ በመውሰድ መረጃውን ያለአግባብ ይፋ ያደረጉ መተግበሪያዎች ይገኙበታል።
ለምሳሌ 'ማይ ፐርሰናሊቲ' የተባለው መተግበሪያ የግለሰቦችን መረጃ ለተመራማሪዎች አሳልፎ ይሰጥ እንደነበረ ተገልጿል።