ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእናቷን አስክሬን ለሦስት ዓመት ቤት ውስጥ ያቆየችው ታሠረች
አሜሪካ፣ ቴክሳስ ውስጥ አንዲት ሴት የእናቷን አስክሬን ለሦስት ዓመታት ቤቷ ውስጥ አስቀምጣ በመገኘቷ በቁጥጥር ሥር ውላለች።
ፓሊስ እንዳለው እናቷ የሞቱት ከሦስት ዓመት በፊት በ71 ዓመታቸው ነው። ከመሞታቸው በፊት ወድቀው የነበረ ቢሆንም፤ ጉዳታቸው ለሞት የሚያደርስ አልነበረም። ሆኖም ልጃቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ ስላላደረግችላቸው ሕይወታቸው አልፏል።
በፖሊስ የተያዘችው ሴት ከልጇ ጋር በምትኖርበት ቤት ውስጥ ሁለት መኝታ ክፍል ነበራት። የእናትየዋ አስክሬን የተገኘው በአንዱ መኝታ ክፍል ወለል ላይ ሲሆን፤ ሌላኛው መኝታ ክፍል እሷና ልጇ የሚተኙበት ነበር።
ከሬሳ ጋር ለሦስት ዓመት ለመኖር የተገደደችው የሴትየዋ ልጅ የ15 ዓመት ታዳጊ ስለሆነች፤ እናትየው ህጻንን አደጋ ላይ በመጣል ተከሳለች።
አሁን ልጅቷ ዘመድ ቤት ተጠግታ ትገኛለች። እናቷ የ20 ዓመት እሥርና የ10 ሺህ ዶላር ቅጣት ሊጣልባት ይችላል።
ሟቿ በአካባቢያቸው ተወዳጅ ሰው ነበሩ። ለሚኖሩበት አካባቢ ጥበቃ ከማድረጋቸው ባሻገር ለ35 ዓመታት አስተምረዋል። ጡረታ ሲወጡ ደግሞ የስፖርት መርሀ ግብሮች መግቢያ ካርኒ ቆራጭ ነበሩ።