ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና ዢንጃን ግዛት ፖሊስ የስልክ መተግበሪያን በመጠቀም ክትትል ያደርጋል ተባለ
የቻይና ፖሊስ የሞባይል መተግበሪያዎችን በመጠቀም በዢንጃን ግዛት የሚኖሩ የዊጎር ጎሳ አባላትን መረጃ ይሰበስባል ሲል ሂይውመን ራይትስ ወች አስታወቀ።
ሐሙስ ይፋ በሆነ ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፤ የሞባይል መተግበሪያው ጥቅም ላይ የዋለው የጎሳው አባላት ጠባይን ለመከታተል፣ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ማኅበራዊ ሕይወት ለመሰለል፣ የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን እንዲሁም ከባህር ማዶ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመከታተል እንደሆነ ተገልጿል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዊጎር ሙስሊሞች በቻይና ከፍተኛ በደል እንደሚደርስባቸው ይገልጻሉ።
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ የዊጎር ሙስሊሞች በዢንጃን ማረሚያ ቤቶች መታሰራቸው መረጃ እንዳለው ገልጿል። የቻይና መንግሥት ግን "የተሀድሶ ትምህርት ማዕከላት" ናቸው ሲል ያስተባብላል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ የቻይና መንግሥት የስልክ መተግበሪያውን የዜጎችን መረጃ ለመመዝገብና ለመሰነድ አገልግሎት ላይ ያውለዋል።
በተጨባጭ 36 አይነት ግለሰቦች ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህም የቤታቸውን የፊት ለፊት መውጪያ በር አልፎ አልፎ የሚጠቀሙ፣ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ያላቸው እንዲሁም ያለ አካባቢው ባለስልጣናት እውቅና ለሐጂ ጉዞ የሚሄዱ ግለሰቦችን ያካትታል።
ከመተግበሪያው የተገኘው መረጃ ቻይና ዜጎቿን ወደምትከታተልበት የማዕከላዊ መንግሥቱ የመረጃ ቋት ውስጥ ይገባል።
እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከሆነ ይህ የማዕከላዊ መንግሥቱ ግለሰቦችን መከታተያ መንገድ "በዓለም ላይ ትልቁ ሰዎችን የመከታተያ ቋት" ነው።
ይህ የመረጃ ቋት ከመንገድ ላይ የደህንነት ካሜራዎች፣ ከነዳጅ ማደያ ስፍራዎች፣ ከትምህርት ቤቶች የሚገኙ መረጃዎችን በመሰብሰብ፤ 'አጠራጣሪ' ባህሪ የሚያሳዩ ግለሰቦች ላይ ባለስልጣናት ክትትል እንዲያደርጉ መረጃ ይሰጣል ተብሏል።
በመላው ቻይና ከ170 ሚሊየን በላይ የመንገድ ላይ ካሜራዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በ2020 ደግሞ 400 ሚሊየን አዳዲስ ካሜራዎች ተተክለው ሥራ ላይ ይውላሉ ተብሏል።
ይህ ቻይና በዓለም ላይ ትልቁ በካሜራ ክትትል ማድረግ የሚያስችል መረብ ለመዘርጋት ያላትኘዕ እቅድ አካል ነው።