ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስሪ ላንካ በደረሰው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ100 ቀነሰ
የስሪ ላንካ ጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ባለፈው እሁድ በደረሰው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ100 የተጋነነ ነው ብለዋል።
ባለፈው እሁድ ነበር ስሪ ላንካውያን ሃገር ሰላም ብለው የፋሲካ በዓልን ሲያከብሩ የነበሩት። ነገር ግን በቀኝ አውለኝ ብለው የጀመሩት ቀን ጥቁር ለበሰ። በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በደረሱ ጥቃቶች ምክንያት።
በወቅቱ የሟቾች ቁጥር 290 ገደማ እንደደረሰ ተዘግቦ ነበር። ትንሽ ቆየት ብሎም ቁጥሩ ወደ 353 እንዳሻቀበ ተነገረ።
አሁን ግን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ በተፈጠረው ግርግር ምክንያት የሟቾችን ቁጥር በትክክል ማስላት ባለመቻሉ ነው ቁጥሩ የተጋነነው ሲሉ ተደምጠዋል።
አሉ በተባሉ ቅንጡ ሆቴሎችና በክርስትና ቤተ-እምነቶች ላይ በተፈፀመው ጥቃት በርካታ የሃገሪቱ ሰዎች እና የውጭ ሃገር ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ፖሊስ ጥቃቱን አድርሰዋል ያላቸውን ዘጠኝ ሰዎች አድኖ ለመያዝ ወዲያ ወዲህ እያለ እንደሆነ አስታውቋል።
ባለሥልጣናት ጥቃቱን የሰነዘረው 'ናሽናል ቶውሂድ ጃማት' የተሰኘውን አክራሪ እስላማዊ ቡድን በሚል እየኮነኑት ይገኛሉ።
አይኤስ የተሰኘው ቡድን በበኩሉ ከጥቃቱ ጀርባ ያለሁት እኔ ነኝ የሚል ተንቀሳቃሽ ምስል ቢለቅም ማስረጃ ግን ሊገኝ አልቻለም።
የስሪ ላንካ መከላከያ ሚኒስትር ሐሙስ ዕለት በገዛ ፍቃዳቸው ራሳቸውን ከሥልጣን ማግለላቸው ሌላ ትልቅ ዜና ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ የደህንነቱ ኃይሉ ጥቃቱን ማስቆም አለመቻሉ ነው።