ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዛምቢያ አባቶች ከትዳር ውጪ ለሚወለዱ ልጆቻቸው የወሊድ ፈቃድ ሊያገኙ አይገባም ተባለ
በዛምቢያ የአሰሪዎች ማህበር መንግሥት ለወንዶች የሚሰጥ የአባትነት የወሊድ ፈቃድ ገደብ እንዲደረግበት ጠየቀ። ማህበሩ ጥያቄውን ያቀረበው ወንዶች የትዳር አጋሬ ብለው ካስመዘገቧት ሴት ውጪ ለሚወልዷቸው ልጆች ፈቃድ እንዳያገኙ በሚል ነው።
ይህ የዛምቢያ የአሰሪዎች ፌዴሬሽን አላማ ያደረገው ወንዶች የሚወስዱትን የወሊድ ፈቃድ ለመገደብ ነው።
የማህበሩ መሪ የሆኑት ሀሪንግተን ቺባንዳ እንዳሉት አንድ ያገባ ወንድ ምን ያህል ጊዜ የአባትነት እረፍት መውሰድ እንዳለበት ገደብ ሊጣልበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የማህበሩ ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ከፀደቀ ያላገቡ ወንዶች እረፍት አያገኙም ማለት ነው።
ወንዶች ከፈለጓት ሴት ሊወልዱ እና አሰሪዎቻቸውን እረፍት ሊጠይቁ ይችላሉ። ነገር ግን አሰሪዎች እረፍት ሊሰጧቸው የሚገባው የትዳር አጋሬ ብለው ካስመዘገቧት ሴት ሲወልዱ ብቻ ነው ብለዋል።
"የሴቶቹ የተለየ ነው እርግዝናቸው ስለሚታይ አያስቸግርም፤ የወንዶቹን ግን ማጣሪያ መንገድ የለንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ሀሳብ አግላይ አይሆንም ወይ ተብለው ሲጠየቁም "አንድ ወንድ ድንገት ብድግ ብሎ 'ልጅ ወልጃለሁ' ብሎ እረፍት ይሰጠኝ የሚለውን ለመከላከል ነው ምክንያቱም ከሥራ በቀረ ቁጥር ሥራ ይበደላል" ብለዋል።
"ከአንድ በላይ የትዳር ጓደኛ ያላቸውም ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል" ሲሉ አክለዋል።
የዛምቢያ የሠራተኞች ህግ ማሻሻያ እየተገደረገበት ሲሆን የሰራተኛ ሚኒስትር ጆይሴ ሲሙኮኮ መንግስት ጉዳዩን እያጤነው እንደሆነ ተናግረዋል።