በኡጋንዳ ፖሊስ ታስረው የነበሩ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ተለቀቁ

በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የቢቢሲ ጋዜጠኞች መለቀቃቸው ተሰማ።

የአካባቢው ባለስልጣናት የጋዜጠኞቹ ቡድን በስፍራው የተገኙበትን ዓላማ በመረዳታቸው ሊለቀቁ እንደቻሉ የቢቢሲዋ ካትሪን ብያሩሃንጋ በትዊተር ገጿ አስታውቃለች።

ጋዜጠኞቹ በፖሊስ የተያዙት ረቡዕ ምሽት ሲሆን ወደ ኡጋንዳ ያቀኑት በመንግስት የሚደረግ ህገወጥ የመድሃኒት ሽያጭን የሚመለከት ዘገባ ለመስራት ነበር።

የኡጋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ጋዜጠኞቹ ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

ምንም እንኳን ፖሊስ ጋዜጠኞቹን ያሰረበትን ምክንያት ባያውቁም ያለ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ጋዜጠኞቹ እንዲለቀቁ ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ በበኩሉ ጋዜጠኞቹ እንዲለቀቁ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር ሲነጋገር ነበር።