ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማህበራዊ መስተጋብር ያፈረጠመው የቤቲ ዋኖስ የኮሜዲ ህይወት
የሁለት ስም ባለቤት ናት፤ እንደ እርሷ አባባል ከሆነ የብርና የብዕር። ቤቲ ዋኖስ እንጀራዋን የምትጋግርበት መጠሪያዋ ሲሆን ቤቴልሄም ጌታቸው ደግሞ ወላጆቿ ያወጡላት፣ ሰነድ የያዘው መጠሪያዋ።
ቤቴልሄም ጌታቸው ገና አፍላ ሳለች የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆና የሚኒ ሚዲያ ክበብ አባል እንደነበረች ታስታውሳለች። ያኔ "መጥፎ ጓደኛ" የሚል የእራሷን ድርሰት ፅፋ በልጆች ዓለም የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ማቅረቧን ትናገራለች።
ቤቲ ድምጿ ወፍራም ስለሆነ በድርሰቱ ላይ ወንድ ሆና ነበር የተወነችው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ፈርጥ የቲያትር ቡድን ውስጥ ከድምፃዊ አብነት አጎናፍር ወንድም ካሳሁን አሰፋ ጋር መተወን ጀመረች።
መርካቶ - "አንድ ህልም ለ20 የሚታይበት ሰፈር"
ቤቲ ልጅነቷን ስታስታውስ ተወልዳ ያደገችበት ሰፈርን አትረሳም። ለሙያዬ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል የምትለው ይህ ሰፈር ችምችም ያሉ ቤቶች የሚገኙበት፣ ማህበራዊ ህይወቱ የተሟሟቀ ነው።
ከአዲስ አበባ የትኛውም አቅጣጫ ሰው ወደ መርካቶ ይፈሳል። ከሀገሪቱ የትኛውም አቅጣጫ ሰው ይጎርፋል። መርካቶ ሞላሁ አትልም፤ ሁሉንም ተቀብላ ማህበራዊ ህይወቷን አዛንቃ ለልጆቿ ታቀብላለች። እንደ ቤቲ ከሆነ ሕይወት በመርካቶ ፈዝዛ አታውቅም። ከነሙሉ ወዟ ትገማሸራለች።
መርካቶ ለሐሜት አትመችም ትላለች ቤቴልሔም። ስሟን በክፉ ከማንሳት በጥበብ ማነሳሳት ይቀላታል። በዚች ትንሿ ኢትዮጵያ ድራማ ያልሆነ ነገር አይታያትም። ትራጀዲ ገጥሞት የሚንሰቀሰቅ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ፣ የሚያፍነከንክ ገጠመኝ ያለው የጎረቤት ልጅ በአውቶብስ ተራ አይጠፋም ባይ ናት።
በመርካቶ ሕይወት ሚስቶ ናት ። የተለያዩ ክልል ሰዎችን አነጋገር ለመቅዳት፣ ኢትዮጵያን ሳይዞሩ ደጃፋቸው ድረስ መጥታ ለመመልከት መርካቶዎች የታደሉ መሆናቸውን ትመሰክራለች።
ጥበብ ናት መርካቶ፣ ጥበበኞችም ሞልተውባታል የምትለው ቤቲ ዋኖስ ኮመዲን እንጀራዬ ያለችው ፕሮ ፕራይድ ውስጥ ነው። ፕሮ ፕራይድ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት የከተማ ድህነትን ለመቀነስና የፀረ ኤች ኤይቪ ስራዎችን ለመስራት መርካቶ ውስጥ እግሩን ሲያስገባ ቤቲ የባህል ቡድኑ አባል ሆና ተቀላቀለች።
"ያኔ እኔም ደምሴም ብቻችንን ነበር የምንሰራው" ትላለች ቤቴልሄም። የሁለቱ ኮመዲያን ለየብቻ መስራት ግን ቡድኑን ያስተባብር ለነበረው ነብዩ ለሚባል ጓደኛቸው አልተዋጠለትም። ሁለቱ ቢጣመሩ አዲስ ነገር እንደሚሆንና ለእነርሱም የሙያ እድገት፣ ለተመልካቾችም አዲስ ነገር ማቅረብ እንደሆነ ተሰማው። እንዲጣመሩ ሀሳብ አቀረበ፤ ሀሳቡን ተቀበሉት።
ዳቦ ባይቆረስም ዋኖሶቹ ተባሉ። "ዋኖስ የወፍ አይነት ናት ሌሎችን ወፎች የምታዝናና" ትላለች ቤቲ።
በ1993 የአለም የኤድስ ቀን እንደ አዲስ አመት ነበር የሚከበረው ትላለች ጊዜውን ስታስታውስ። ትልልቅ ዝግጅቶች በየአዳራሹ፣ ድንኳኖች በየቀበሌው ተጥለው፣ ግድግዳዎች በተለያዩ ፖስተሮች አጊጠው፣ ቲሸርት፣ ኮፍያ ተዘጋጅቶ ሙዚቃ፣ ጭውውት እየቀረበ ይከበር ነበር።
እርሷ ታዲያ ያኔ ፕሮፕራይድ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ከሽመልስ በቀለ ጋር መድረክ የመምራት እድል አገኘች። ሽመልስ አደነቃት። በፊትም የጥበብ ጥሪ አለኝ ብላ በየመድረኩ ላይ መክሊቷን ትፈልግ ነበር የዛን እለት አገኘችው። ኮመዲያን ቤቴሊሄም ጌታቸው በኮሜዲ አለም ስሟን ፃፈች።
ቀጣዩ ስራ የተፃፈው ስሟ በጊዜ ድሪቶ እንዳይደበዝዝ ተግቶ መስራት ነው። ለዚህ ደግሞ የዋኖሶች አዲስ ጥምረት አገልግሏታል። የዋኖሶችን አዲስ ጥምረት በትርኢት መካከል መፈተን ሲፈልጉ ደግሞ ሜጋ የኪነጥበባት ማዕከል መድረክ አገኙ።
19 94 አ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ምሽት ዋኖሶቹ አዲስ የኮመዲያን ጥንዶች ሆነው ብቅ አሉ። የአድማጭ ተመልካቹ ምላሽም የሞራል ስንቅ ሆኖ ለቀጣይ ጉዟቸው አገዛቸው። ያኔ የነበረውን ጊዜ ስታስታውስ "ቀልድ ይደገም ተብሎ አያቅም፤ ያኔ ግን ይደገም ሁሉ ተብሎ ደግመን አቅርበናል" ትላለች።
ዋኖሶቹ፣ በዘመኑ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኮመዲያን አለባቸው ተካ በሚቀርበው አለቤ ሾው ላይ ሲቀርቡ ደግሞ መልካቸውም ስማቸውም በአድናቂዎቻቸው ትዝታ ውስጥ ታተመ።
ሽመልስ በቀለም በትርኢቱ ላይ ካያት በኋላ መክሊቷን አውጥታ መጠቀም መጀመሯን አንስቶ አበረታታት። ይህ ማበረታቻ በስራዋ ብርቱ መሰረት እንደሆናት ትናገራለች።
የዋኖሶቹ ጥምረት
የኢትዮጵያ የጥበብ አድባር በታዳሚዎቹ ላይ የሳቅ ሸማ የሚደርቡ ከያኒያንን አብቅላለች። በየጭውውቱ፣ በየቴያትር መድረኩ ለተመልካች የሳቅ ቀለብ የሚሰፍሩ ባለሙያዎች አልጠፉም። እንግዳ ዘር ነጋ፣ በላይነሽ አመዴ፣ ዘነበች ጭራ ቀረሽ አፈሩን ያቅልላቸው ተብለው ጎልተው የሚጠቀሱ ጎምቱ ባለሙያዎች ናቸው።
እነዚህን የጥበብ ባለሙያዎች ያበቀለች አድባር ግን ማህፀኗ ሴት ስታንዳፕ ኮመዲያን ያፈራ አይመስልም። የስታንዳፕ ኮመዲያኑ ዘርፍ የሴት ኮመዲያን ድርቅ የመታው ነው።
ቤቲ "በርግጥ ኮመዲን በጭውውት መልክ የሚሰሩ ነበሩን። በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ እነ እንግዳዘር ነጋ የነበራቸው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም። እነበላይነሽ አመዴ እነ ጭራ ቀረሽ በየትያትር መድረኩ ላይ ተክነውበት አፍነክንከውናል። ስታንዳፕ ኮመዲያን ግን አልነበረንም" ትላለች።
እርሷ ከኮሜዲያን ደምሴ ጋር ተጣምራ ስትመጣ የመጀመሪያዋ ሴት ስታንዳፕ ኮመዲያን ሆነች።
ደምሴና እርሷ ሲመጡ አዲስ ሆነው ጥምረታቸው ተወዳጅነት አፈራ። ሴት ስታንድ አፕ ኮመዲያን ባልተለመደበት ሀገር አይኖች ሁሉ ቤቲ ዋኖስ ላይ አረፉ። ይህ ጥምረት ግን ብዙ አልቆየም፤ ከሙያ አጋሯ ጋር ባለመግባባት ተቋጨ።
ኩምድናና ሴትነት
ቤቲ ከሙያ አጋሯ ጋር ከተለያየች በኋላ በየመድረኩ ደጋግመን አላየናትም። ምነው ተብላ ስትጠየቅ ልጅ መውለድና ማሳደግ ባተሌ አድርጓት እንደነበር ትገልፃለች። ከዚያ በኋላ ግን ትንንሽ ጸሐዮች የሬዲዮ ድራማ ላይ በመሳተፍና የራሷን ስራዎች በመስራት ላይ ትገኛለች።
በሳቅ ገበታ ላይ ወንድ ኮሜዲያን ተሰብስበው የድርሻቸውን ሲቋደሱ ሴቶችን አለማየታችን ስለምን ነው? ብለን ጠይቀናል። ኮመዲ ለሴቶች ፈታኝ ነው የምትለው ቤቴልሄም አንዱ ልፋት መጠየቁ ነው ስትል ታስረዳለች።
"ኮመዲን አቅልሎ ማየት፣ በዙሪያ ያሉ ወዳጆች፣ ጓደኞችና ቤተሰብ ስለሳቁ ሰፊውን ጀማ አስቃለሁ ብሎ መዘናጋት ሴትነት ላይ ሲታከልበት ፈታኝ ያደርገዋል።"
ሌላው በመጀመሪያው መድረክ ሳይሳካ ሲቀር ደንግጦ መቅረት፣ ረዥም መንገድ ለመሄድ፣ መውደቅ መነሳቶችን ለማለፍ ቅስም ማጣት ሴት ኮመዲያንን እንዳናይ አድርጎናል ባይ ናት።
ሴት በቤት ውስጥ፣ በማህበረሰቡ መካከል ጭምት እንድትሆን በሚፈለግበት ባህል ውስጥ ልል የሆነ ማህበራዊ መስተጋብር የሴት ኮሜዲያን ሌላ ፈተና ነው ስትልም ተጨማሪ ነጥቦችን ትዘረዝራለች።
"እኔ ግርግር እወዳለሁ። መርካቶ እንኳን ባልሆን የራሴን መርካቶ በየሄድኩበት እፈጥራለሁ" የምትለው ቤቴልሄም የማህበራዊ መስተጋብርን አስፈላጊነት አጽንኦት ትሰጠዋለች።
"ኮመዲ የጤፍ ዝናብ ነው" የምትለው ቤቲ "የጤፍ ዝናብ ሲወርድ ትንንሽ ነው፤ ምን ያህል እንደበሰበስክ የምታውቀው መድረሻህ ላይ ስትሆን ነው። ለኮመዲም የማህበራዊ ህይወት ግብዓት ጠንካራ ከሆነ ከህይወት ልምድና ከማህበራዊ መስተጋብር የሚቃረመው ትንንሽ ነገር በበቂ ሁኔታ ማቆሩ የሚታወቀው ከህዝብ ፊት ቀርቦ ምላሽ ሲገኝ ነው" ባይ ናት።
ፈጠራ የሴት ኮመዲያን ጉልበት መሆን አለበት ስትል ኮሜዲያንነትን መክሊታቸው ለማድረግ ለሚፈልጉ ሴቶች ተጨማሪ ነጥቦችን ትጠቅሳለች።
"ዓለምን ወንዶች ከሚያዩበት ውጪ ማየት፣ ነገሮችን በግልባጩ በመረዳት ከእያንዳንዱ የህይወት ዘለላ የሳቅ ቅንጣት መፈለግ ያስፈልጋል" ትላለች።
ማህበረሰቡ ሴትን ፈጣጣ ናት ሲል ያሸማቅቃል የምትለው ቤቲ "አይናፋር ሆኖ ኩምድና ስለማይታሰብ፣ አንገትን ቀና አእምሮን ሰላ ማድረግ ለሴት ኮመዲያን አስፈላጊ ነው።"
ሌላው ከሙያ አጋሮች የሚመጣ ግፊያን ጉሽሚያ መቋቋም እንደሚያስፈልግም ትመክራለች። ሴት አጋዥ እንጂ፣ ራሷን ችላ መድረክ ላይ እንድትቆም የማይፈልጉ የሙያ ባልደረቦች ሊገጥሙ እንደሚችሉ ታስታውሳለች።
የኮሜዲያን ኑሮ እንደቀልድ ስለሚታይ ለየትኛውም ቁምነገር አለመታሰባቸው፣ እንደ ዋዛ፣ ፈዛዛ፣ ቧልት ወዳድ፣ መቆጠር ለሴቶች ይበልጥ ፈታኝ መሆኑንም ትጠቅሳለች።
መውለድና የኮሜዲ ህይወት
ከዚህ በፊት መስመር የለቀቁ ቀልዶች ከነበሩኝ ዛሬ ልጅ ኖሮኝ አላስባቸውም የምትለው ቤቲ ልጅ ኃላፊነትን ይዞ ይመጣል ስትል ከወለደች በኋላ በስራ ህይወቷ ላይ ያለውን ለውጥ ትናገራለች። የራስን ልጅ በማሰብ መስመሩን ያልሳተ ቀልድ ለማቅረብ እንደምትታገልም ስታስረዳ በዝግጅቷ ውስጥ ልጇን ማዕከል እንደምታደርግ ስታብራራ "ልጆች ራሳቸው የቀልድ አቀባዮች ይሆናሉ" በማለት ነው።
ከልጇ ጋር ስትጫወት የኮመዲ ሀሳቦችን እንደምታገኝ የምትናገረው ቤቲ ዋኖስ ስራዎቿን ስታቀርብ መጀመሪያ ራሷ መሳቅ እንዳለባት በመቀጠል ጓደኞቿ ከዛም ለልጇ በማውራት ምላሻቸውን ለማግኘት እንደምትሞክር ትገልፃለች።
ቤቲ ዋኖስ በዩ ቲዮብ የሚቀርብ የኮመዲ ስራ፣ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ እና የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ለመስራት ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ነግራናለች።