ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማሊ 37 ሰዎች ገደማ በታጣቂ ተገደሉ የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች
ማሊ
ዛሬ በማዕከላዊ ማሊ አንድ ታጣቂ በከፈተው ተኩስ ወደ 37 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል። መንግሥት ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል። ተኩሱ የተከፈተበት አካባቢም የጸጥታ ሀይሎች ልኳል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
የአፍሪካ ኅብረት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምርጫ ከጥቂት መሰናክሎች ውጪ ሰለማዊ ነበር ብሏል። የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ መንግሥት የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲመልስ ጠይቋል። የኮንጎን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ከሰኞ ጀምሮ ኢንተርኔት እንደተቋረጠ ነው።
ሕንድ
ሁለት ሕንዳውያን ለሴቶች የተከለከለ ቤተ አምልኮ ውስጥ በመግባት ታሪክ ሰርተዋል። በቅርቡ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ሴቶች ወደ ቤተ አምልኮው እንዲገቡ ቢፈቅድም በርካታ ተቃዋሚዎች ሴቶች እንዳይገቡ ሲከላከሉ ነበር።
ጀርመን
ጣልያን- ፍሎረንስ ውስጥ የሚገኝ የሥነ ጥበብ ጋለሪ የናዚ ወታደሮች ሰርቀው ጀርመን የወሰዱት ሥዕል እንዲመለስ ጠይቋል። ከ76 ዓመት በፊት የተሰረቀው ሥዕል በጀርመናዊ ቤተሰብ መኖሪያ ውስጥ ይገኛል።
ሳዑዲ አረቢያ
ሳዑዲ አረቢያ ሀሰን ሚናዥ በተባለ አሜሪካዊ ኮሜዲያን የተሰራ መሰናዶ ከድረ ገጽ እንዲሰረዝ አደረገች። አሜሪካ ውስጥ የተቀረጸው መሰናዶ ከጋዜጠኛ ካሾግጂ አሟሟት ጋር በተያያዘ ሳዑዲን የሚተች ነው።
አሜሪካ
አሜሪካ- ሳንታ ሞኒካ ውስጥ የሚገኝ አንድ የቴክኖሎጂ ተቋም ሙሉ በሙሉ የአዕምሮ ዝግመት ያለባቸው ሠራተኞችን ቀጥሯል። አዕምሮ ዘገምተኛች የሚደርስባቸውን መገለል ለመስበር የሚረዳ እርምጃ ነው ተብሏል።
የአውሮፕላን አደጋ
የአውሮፓውያኑ 2018 የአውሮፕላን አደጋ ቁጥር የጨመረበት መሆኑን ኤኤስኤን የተባለ የኔዘርላንድ ድርጅት ተናገረ። በ2017 በአውሮፕላን አደጋ የሚቱት 44 ሰዎች ብቻ ናቸው። ባሳለፍነው 2018 ግን 18 አፈጋ ተከስቶ 556 ሰዎች ሞተዋል።
እንግሊዝ
እንግሊዝ ውስጥ በ2018 የመጀመሪያ ቀን አንድ ግለሰብ 115 ሚሊዮን ፓውንድ ማለትም ወደ 4 ቢሊዮን ብር ገደማ ሎተሪ ደርሶታል። የሀገሪቱ ብሔራዊ የሎተሪ ድርጅት እንዳስታወቀው በድርጅቱ ታሪክ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ገንዘብ እጣ ሲደርስ ይህ አራተኛው ነው።
ቻይና
ቻይና የሮቦት ስፔስሺፕ በጨረቃ ላይ ለማሳረፍ እየተዘጋጀች ነው። የመጀመሪያ የሆነው ስፔስሺፕ በቀጣይ ቀናት እንደሚላክ ለቻይና መንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል።