ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞ የአልሸባብ መሪ በኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ በቁጥጥር ሥር ዋለ
የሶማሊያን ደቡብ ምዕራብ ግዛት ለማስተዳደር እየተወዳደረ የሚገኘው የቀድሞው የአልሸባብ መስራች እና አባል ሙክታር ሮቦው በሶማሊያዋ ባይዶዋ ከተማ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ሙክታር ሮቦው በቀጣዩ ሳምንት የሚካሄደውን ምርጫ በማሸነፍ የሶማሊያን ደቡብ ምዕራብ ግዛት ሊያስተዳድሩ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱ እጩዎች መካከል አንዱ ነበር።
ሙክታር ሮቦው ዛሬ ጠዋት በባይዶዋ በታጣቂዎች እና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።
ይህንንም ተከትሎ በከተማዋ የቴሌኮም አውታሮች የተቋረጡ ሲሆን፤ እስካሁን ሙክታር ሮቦው ለምን በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።
ቢቢሲ ሶማሊኛ ያነጋገራቸው የሶማሊያ ፓርላማ አባላት እንዳረጋገጡ የአሚሶም የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል በሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ነው ሙክታር ሮቦን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት።
የቀድሞ የአልሸባብ መሪ እና መስራች ከሁለት ወራት በፊት ግዛቶችን ለማስተዳደር በምርጫ ለመሳተፍ ያቀረቡትን ጥያቄ የሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ፍቃድ ቢነፍግም የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ግን በምርጫው እንዲሳተፉ ፈቅዷል።
ሙክታር ሮቦው የሶማሊያ የፌደራል መንግሥት በደቡብ ምዕራብ ተሰሚነት እንዳይኖረው ክፍተኛ ጫና ያሳድራሉ።
አንዳንዶች ሙክታር ሮቦው አልሸባብን ለመውጋት ሁነኛ ሰዎች ናቸው ሲሉ፤ ሌሎች በበኩላቸው ሙክታር ከዚህ ቀደም ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር በነበራቸው ታሪክ ምክንያት በጥርጣሬ ይመለከቷቸዋል።
ሙክታር ዛሬ ማለዳ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉ ታዋቂነቱን ክፍ የሚያደርገው ሲሆን፤ በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና ተባባሪው የውጪ ሃገራት ላይ ግን ጥላቻን ይጨምራል የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ሙክታር ከአልሸባብ ኃላፊነቱን እራሱን ማግለሉን በማሳወቅ የሶማሊያ ሕዝብ ይቅርታ ያድርግልኝ ሲል ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ዕርቅ ለማውረድ ሞክሮ ነበር።
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የአሚሶም የጸጥታ አስከባሪ አባላት ከኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ቡሩንዲ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የተወጣጡ የጦር አባላት አሉት።