ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ የምክር ቤት ምርጫ ዲሞክራቶች ቢያሸንፉ ትራምፕ ሊከሰሱ ይችላሉ?
የአሜሪካ ምርጫ ማብቂያ ያለው አይመስልም። ለጊዜው ዋና ዋና ነጥቦችን ብናነሳ አይከፋም።
የ"ሚድ-ተርም" ምርጫ ምንድነው?
'ሚድ-ተርም' የተባለው መሀል ላይ ስለሚካሄድ ነው። ለአራት ዓመት እንዲያገለግል የተመረጠው ፕሬዚዳንት ሁለት ዓመት እንደቆየ የሥራ ዘመኑ ይጋመሳል። በዚህ ወቅት "ሚድ-ተርም" ምርጫ ይከሰታል። ምርጫው ታዲያ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በወርሃ ኖቬምበር (ኅዳር) ነው የሚካሄደው።
ምን ዓይነት ምርጫ ነው?
የአሜሪካ ምክር ቤት ላዕላይና ታህታይ ምክር ቤቶች አሉት፤ የአማርኛ ስያሜያቸው ሊያከራክር ቢችልም። ታህታዩ ምክር ቤት 435 የሕዝብ እንደራሴዎች ሲኖሩት 'ሀውስ ኦፍ ሪፕረዘንታቲቭስ' ይባላል፤ ላዕላዩ ምክር ቤት 100 አባላት ሲኖሩት ተመራጮቹ ሴናተሮች ተብለው ይጠራሉ።
የኅብረት ስማቸው ኮንግረስ ነው። ይህ ሕግ አውጪ ምክር ቤት በድምሩ 535 አባላት ይኖሩታል።
በደፈናው አንድ ረቂቅ ሕግ ከላዕላዩም ከታህታዩም ምክር ቤት ሊመነጭ ይችላል ማለት እንችላለን።
የሁለቱ ምክር ቤቶች ልዩነት ታዲያ ምንድነው?
የቅርጽም የግብርም ልዩነቶች አሏቸው። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ለምሳሌ በውክልና ይለያያሉ። ግዛቶች የታህታይ ምክር ቤቱ ውክልናቸው እንደ ሕዝብ ስፋታቸው ይወሰናል። በብዙ የሕዝብ እንደራሴ የሚወከሉ እንደ ካሊፎርኒያ ያሉ ግዛቶች 53 የሚደርሱ ተወካዮች እንዳሏቸው ሁሉ በአንድ አባል የሚወከሉ እንደ አላስካ ያሉ ትንንሽ ግዛቶች ደግሞ አሉ።
ዋናው ነጥብ የታህታይ ምክር ቤት ውክልናው በሕዝብ ቁጥር ከመሆኑ ላይ ነው።
በላእላይ ምክር ቤት ግን ሁሉም ግዛቶች በሁለት-በሁለት አባላት ይወከላሉ። የሕዝብ ቁጥራቸው የተለየ ነገር አያስገኝላቸውም።
ሁለቱን ምክር ቤቶች ከሚለይዋቸው ነጥቦች ሌላው የአገልግሎት ዘመን ነው።
ሴናተሮች የሚመረጡት ለ6 ዓመታት እንዲያገለግሉ ነው። የሕዝብ እንደራሴዎች ግን ለሁለት ዓመት።
የዘንድሮ ምርጫ ለምን አጓጊ ሆነ?
የዛሬው ምርጫ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የሚካሄድ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ተወስዷል። ለምን?
አንዱ ምክንያት ሁለቱም የምክር ቤት ወንበሮች በሪፐብሊካን ወኪሎች አብላጫ ተይዘው መቆየታቸው ነው። ወንበሮቹ ከሪፐብሊካን እጅ ከወጡ ትራምፕ ጉድ ይፈላባቸዋል።
ነገሩ ሁሉ ቅድመ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሄደ በትራምፕ የተቆጡ ድምጽ ሰጪዎች በነቂስ ወጥተው ለዲሞክራቶች ድምጻቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ማንም ሊገምት እንደሚችለው ዶናልድ ትራምፕ ግብታዊ ውሳኔዎቻቸውን ለማጸደቅ ምጥ ይሆንባቸዋል?
ለምሳሌ ከሜክሲኮ ጋር ድንበር የመገንባቱን ሐሳብ ኮንግረሱ ካላጸደቀው ትራምፕ አንዲት ጡብ ማስቀመጥ አይችሉም።
ዲሞክራቶች ቢያሸንፉ ትራምፕ ሊከሰሱ ይችላሉ?
አያደርጉትም አይባልም። ሰውየው ከራሺያ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሴቶች ላይ በሚሰነዝሯቸው መልካም ያልሆኑ አንደበቶች ተብጠልጥለዋል።
እርግጥ ነው እስከዛሬ ዲሞክራቶች ስለ ሰውየው መከሰስ ጉዳይ በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል።
እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ቢነሳና ፕሬዝዳንቱን የሚያስከስስ ጭብጥ ቢገጥም ግን የክስ ድምጽ ሊሰጡባቸው ይችላሉ።
በ1998 እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ክሊንተን ሕግን በማደናቀፍ ወንጀል እንዲከሰሱ ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንደነበር ይታወሳል። በአብላጫ ድምጽ ባያልፍም።
አይበለውና ተመሳሳይ ነገር በዶናልድ ትራምፕ ቢነሳና ከመቶ ሴናተሮች ሦስት እጁ ይከሰሱ ብሎ ድምጽ ቢሰጥ አሜሪካ በምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ልትመራ የምትችልበት ዕድል ጠባብ አይደለም።