ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዕውቁ ፈረንሲያዊ ገጣሚ ሻርል ቦድሌር የኑዛዜ ወረቀት በጨረታ ተሸጠ
የፈረንሳይ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ገጠሚ የነበረው ሻርል ቦድሌር ራሱን እንደሚያጠፋ የፃፈበት ብጣሽ ወረቀት 7.3 ሚሊየን ብር በጨረታ ተሽጧል።
ማስታወሻው የተፃፈው እኤአ ሰኔ 30 1845 ሲሆን የተፃፈውም ለፍቅረኛው ዣን ዱቫል ነው።
ገጣሚው ያኔ 24 ዓመቱ የነበረ ሲሆን ደብዳቤውን በፃፈ ዕለት ራሱን ለማጥፋት ሞክሮ ተርፏል።
እንዲህ አይነት ጨረታዎችን የሚያስተዋውቀው ኦዝና ድረ ገፅ ደብዳቤው ለአንድ ግለሰብ የተሸጠው ከተገመተለት ዋጋ ሶስት እጥፍ በላይ መሆኑን ገልጿል።
በዚህ ደብዳቤው ላይ ለፍቅረኛው "ይህ ደብዳቤ ሲደርስሽ ሞቻለሁ" ሲል ራሱን ማጥፋቱን ገልጾበታል።
"ራሴን የማጠፋው ዳግም የመኖር ፍላጎቴ ከወስጤ ስለተሟጠጠ ወይም ተኝቶ መነሳት ስለታከተኝ ነው" በማለት በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።
ቡድሌ በውርስ ያገኘውን ገንዘብ አባክኖ ችግር ውስጥ ከተዘፈቀ በኋላ ደረቱን በመውጋት ራሱን ለማጥፋት የሞከረ ሲሆን ሙከራው ግን ለከፋ ጉዳት ሳይዳርገው ቀርቷል።
እራሱን ለማጥፋት ከሞከረበት ዕለት በኋላ ለ22 ዓመታት ኖሯል። 'ሌ ፍለር ዱ ማል' በተሰኘው ተከታታይ ጽሁፎቹ ዝናው እጅግ ናኝቶ ነበር።
የግጥም ስራዎቹ በፈረንሳይ ሥነ-ጽሁፍ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል የሚባልለት ሻርል ቦድሌር 1867 ላይ በአባላዘር በሽታ ህይወቱ አልፏል።