ኢትዮጵያ 8.5 በመቶ ዕድገት ታሥመዘግባለች፡ አይ.ኤም.ኤፍ.

አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, Sean Gallup

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ.) ከፍተኛ ኃላፊዎች ለሁለት ሳምንታት ያክል የቆየ ጉብኝት በኢትዮጵያ አድርገው ተመልሰዋል።

በጉብኝታቸው መጨረሻ ላይም ኢትዮጵያ ከ2018/19 ባለው የፈረንጆቹ ዓመት የ8.5 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ ትንበያቸውን አስቀምጠዋል።

ድርጅቱ ትንበያውን ለማስቀመጥ ከተመለከታቸው መስፈርቶች መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር በቅርቡ ተግባራዊ እንዲደረግ ያዘዘው በመንግሥት ስር የነበሩ ተቋማትን ለግል ባለሃብቶች በሽያጭ መልክ ማዘጋጀት አንዱ ነው።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ሰኢድ ኑሩ የኢኮኖሚው እድገት ተስፋ ያለው ሆኖ መቀመጡ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመሳብ አስተዋፅኦ ያደርጋል ይላሉ።

«ፖለቲካው ከተረጋጋ እና ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት አመቺ ነች ተብሎ ተስፋ ከተደረገ እንደባለፉት ዓመታት ከ10 በላይ ባይሆንም 8.5 በመቶ ማደግ ይቻላል ብለው ያሰቡ ይመስለኛል» ሲሉ መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ዶ/ር ሰዒድ ድርጅቱ እያንዳንዱን ዘርፍ በዝርዝር አስቀምጦ ትንታኔ ስላልሰጠ አስተያየት ለመስጠትም ከባድ ነው በማለት፤ «ባሉት ነባራዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርተው ባለሙያዎቹ የራሳቸውን ትንበያ ይሰጣሉ፤ መረጃውንም ከመንግሥት ይጋራሉ ብዬ አስባለሁ» ይላሉ።

እንደ ዶ/ር ሰዒድ ሁሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተኬ ዓለሙ «ዋናው ነገር ሰላም ነው» ብለዋል።

«አይ.ኤም.ኤፍን የመሳሰሉ ድርጅቶቹ ተዓማኒነታቸው አያጠራጥርም፤ ከባዱ ነገር ተፈፃሚነቱ ላይ ነው እንጅ» ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተኬ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ተኬ «እነ አሜሪካ ቢሆኑ ይህ ትልቅ አሃዝ ነው፤ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ግን 8.5 በመቶ ዕድገት ትልቅ የሚባል አይደለም» ይላሉ። «ይህ እንዳይሆን ሊያግደው የሚችለው ዋነኛው ነገር አለመረጋጋት ነው እንጅ 8.5 በመቶ እድገት በዓመት ያን ያህል ትልቅ ቁጥር ሆኖ ላይሳካ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት አይደለም» ይላሉ።

በመንግሥት ስር የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ባለሃብቶች የማዘዋወሩ ጉዳይ አጨቃጫቂነቱ የቀጠለ ይመስላል።

«የመንግሥት ንበረቶች ገና ወደግል ባለሃብቶች ተሸጋግረው ምጣኔ ሃብቱ ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦና እውነተኛው ውጤት እስኪታይ ድረስ ከሁለት ዓመት በላይ ሊፈጅ ይችላል» የዶ/ር ሰዒድ ሃሳብ ነው።

የመንግስት ድርጀቶቹ ገና ወደ ግሉ ዘርፍ ዞረው የረጅም ጊዜ ውጤቱ እስኪታይ ድረስና ውሳኔው ትክክለኛና ውጤታማ ይሆናል አይሆንም የሚለውን ለመወሰን ጊዜው ገና ነው።

እንደውም ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ድርጅቶቹ ከዚህ በኋላ ተጨማሪ እሴት ይዘው ይመጣሉ ወይ? ሌላውን የኢኮኖሚ ዘርፍ ማቀላጠፍ የሚችል ብቃት ይኖራቸዋል ወይ? መሆን አለበት ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አለማቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶችና ሃገራት ብዙ እዳ መሸከሟና የጀመረቻቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለመቻላቸው እየታየ ሃገሪቱ በዚህ ያክል ቁጥር ታድጋለች ብሎ መገመት ይቻላል ወይ? ለዶ/ር ሰኢድ ያቀረብናለቸው ጥያቄ ነው።

አይ ኤም ኤፍ ተስማማበትም አልተስማማበትም የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ለማስጨረስ ገንዘብ ማግኘት ካቃተው፤ ከኤክስፖርት መቀነስ ጋር ተያይዞ ካጋጠመው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ጎን ለጎን የብድር ጫናው በራሱ የሚያገኘውን የውጪ ምንዛሪ ይቀንሳል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተባለውን 8.5 በመቶ እድገት ማስመዝገብ አስቸጋሪ ነው።

ተአምራዊ እድገት ሊመጣ አይችልም ሲሉ ድርጅቱ ያስቀመጠውን ትንበያ ማሳከት ለኢትዮጵያ ሊከብድ እንደሚችል ጠቁመዋል።