1 ቢሊየን ዶላሩ ስንት ችግር ያስታግሳል?

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
በእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ውስጥ የጀበና ቡና እፉት እያሉ የሚያወጉ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መሪዎችን ምስል የተመለከተ አንዳች መልካም ድባብ በመሪዎቹ መካከል እንዳቆጠቆጠ ይገምታል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የተባባሩት አረብ ኤምሬትስ ልዑል ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ቆይታ በሰናይ ውጤት ለመደመደሙ የተሻለ ፍንጭ የሚሰጠን ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ሺዴ በኩል የተሰጠው የድህረ - ምክክር መግለጫ ነው፡፡
የተባባሩት አረብ ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ የ3 ቢሊየን ዶላር እርዳታ እና መዋዕለ-ንዋይ ድጋፍ ለማድረግ ፈቅዳለች፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊየን ዶላሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ እንደሚደረግ እና ሀገሪቱ የገባችበትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማረጋጋት አንደሚውል የመንግስት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አህመድ ሺዴ ለውጭ ሀገራት የዜና አውታሮች አስታውቀዋል፡፡
የችግሩ ግዝፈትና የተባባሩት ዓረብ ኤምሬትስ ችሮታ
የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያዋ ከዕለት ተዕለት እየመነመነ በመምጣቱ መሠረታዊ እና አንገብጋቢ ግብዓቶችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት ለቸገራት ኢትዮጵያ፣ የተባባሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሰሞነኛ "ደራሽነት" የተወሰነ እፎይታን እንደሚሰጥ ይታመናል፡፡
ለምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ተንታኙና የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ አቶ ዘሪሁን ተስፋዬ የተገኘው ገቢ በቋፍ ላይ ላለው ምጣኔ ሃብታችን ማስታገሻ ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከወር ብዙም ላልተሻገረ ጊዜ ብቻ ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ሸቀጦችን መግዣ ተቀማጭ እንዳላት ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡
የአሁኑ ገንዘብ ለዘላቂነት ከሙሉ ችግሯ ሙሉ በሙሉ እንደማያወጣት የሚናገረው አቶ ዘሪሁን "መድኃኒትን የመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ ሸቀጦችን ለማስገባት አቅም ይሆናታል፤ እንደ ጥቃቅን ወጪዎች መሸፈኛ ወይንም ማነቃቂያ ብናየው ይሻላል›› ይላል ፡፡
በርግጥም ባሳለፍነው ጥር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ይፋ ባደረገው ሪፖርት በ2016/17 የበጀት ዓመት ማብቂያ ኢትዮጵያ የነበራት የውጭ ምንዛሬ ተቀማጭ 3.2 ቢሊየን ነበር፡፡ የአሁኑ የኤመሬቶች ድጋፍ እና የመዋዕለ-ንዋይ ድጋፍ ተጠቃሎ ሲገባ ተቀማጩን በእጥፍ ያሳድጋል፡፡
የምጣኔ ሐብት ጉዳዮች ተንታኝና አጥኚ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ከአቶ ዘሪሁን ጋር የሚስማማ ምልከታ አላቸው፡፡
በአሁኑ ገንዘብ የተወሰኑ ወራት የገበያ ዕድሜ መግዛት ይቻል ይሆናል ፤ሆኖም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚን መታደግ የሚቻለው ለሁለት አበይት ችግሮች መፍትሄ ሲገኝ እንደሆነ ይዘረዝራሉ፡፡
በዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ምልከታ፣ የሀገሪቱ የተሳሳተ የፋይናንስ ሥርዓትና አመራር ሀገሪቱን ለምጣኔ ሀብታዊ አጣብቂኝ ካበቁ ምክንያች አንዱ ነው፡፡
የፋይናንስ አስተዳደሩ በአጠቃላይ የተያዘው በብሔራዊ ባንክ ነው የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ "ለዓመታት ማሻሻያ ባልተደረገለት ሥርዓት ውስጥ የውጪ ባንኮች ተቀማጭ ይዘው የሚገቡበት ዕድል የለም፡፡በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ስትጠቀምበት የነበረው (ዶላር) ከዲያስፖራው (ሀዋላ)እና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በብድር የተገኘ ነበር" በማለት ያስገነዝባሉ፡፡
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ገብተው እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ "በነፃ ሀገራቸውን ለማገልገል ፈቃደኛ እስከ መሆን ፍላጎት ያላቸውን" ውጤታማ ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሀብት ሊቆችን አስተባብሮ አዲስ እና የተሻለ የፋይናንስ ሥርዓት ዝርጋታ ማስተዋወቅ መፍትሔ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ቁጥራቸው የበዙት ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከሚፈጁት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አንጻር ሌላኛ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፈተና መሆናቸውን ተንታኙ በሁለተኛ ችግርነት ያነሳሉ፡፡
የአንዳንዶቹ ግንባታ መልካም መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የብዙ ግንባታዎች ክንውን ግን የብክነት ምንጭ ስለመሆኑ ፣ይሄም በተራው ሀገሪቱ የነበራትን የዶላር ክምችት አሟጣ እንድትጠቀም እንዳስገደዳት ሲያስረዱ "ለምሳሌ 11 የስኳር ፋብሪካዎች ይሰራሉ ተብሎ ነበር"ይላሉ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ።
በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፈስሶባቸው የውሃ ሽታ ሆነው የቀሩ ‹ፕሮጀክቶችን› እያስታወሱ፣ "እነዚህ ግንባታዎች አልተሳኩም፡፡ በእነዚህ ግንባታዎች ላይ የሚወጣው ገንዘብ ካለ ውጤት በደፈናው የሚፈስ ከሆነ ቢቆሙ ይሻላል፡፡ እንዲያው ቀደም ብሎ ነበር ይሄ ርምጃ መወሰድ ያለበት፡፡ በተመሳሳይ ውጤት ያላሳዩ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታን ጋብ ማድረግ ያስፈልጋል" ይላሉ።
የፋይናንስ አስተዳደሩን የሚመሩት ሰዎች ብቃት ሌላው ቁልፍ ነጥብ ነው። የፋይናንስ ተቆጣጣሪ አካል ውስጥ ብቃት ያላቸው ዜጎችን ማሳተፍ ያሻል ይላሉ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ።
"ብዙ ብቁ ዜጎች አሉን። አምስት ኢትዮጵያዊያን የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ ናቸው። የአይኤምኤፍ የአፍሪካ ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊ ናቸው። አሜሪካ አገር ትልልቅ ኮርፖቴሽኖችን የሚመሩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ለአንድ ዓመት ለሁለት ዓመት አገራችን ያለ ደመወዝ እንኳ ሥሩ ቢባሉ ደስ የሚላቸው ናቸው።"

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
የመዋዕለ-ንዋይ ድጋፍ እና የሰጥቶ መቀበል ጥያቄ
አቶ ዘሪሁን ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያገኘችውን መዋዕለ-ንዋይ ድጋፍ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ተቋም ዛሬ በኢኮኖሚ ለበረቱ የትናንት ታዳጊ ሀገራት ከጥቂት ዐስርት ዓመታት በፊት ሲያደርጉ እንደነበረ ያወሳል።
"የልማት ብድር ተደረገ የሚባለው ተቋማት ወይንም ሀገራት ለአንድ የተወሰነ ጉዳይ አሊያም የልማት ሥራ አንደኛው ለሌላኛው ወገን ከገበያ ምጣኔ በወረደ ወለድ ሲያቀርቡ ነው፡፡" ይላል።
በተለይ በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ እና 80ዎቹ ህንድና ቻይናን ለመሰሉ የእስያ ሀገራት፤ ከ1990ዎቹ ወዲህ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራትን ምጣኔ ሃብት ለማበረታት በሥራ እንደዋለ የሚጠቅሰው አቶ ዘሪሁን ይሄ ብድር ከሌሎች ብድሮች ለየት ባለ መልኩ ለሀገራት የሚሠጠውን አንጻራዊ እፎይታ ያነሳል፡፡
ሆኖም ብድር በተፈጥሮው በሀገራት ላይ ከሚተወው የወለድ እና ፖለቲካዊ ጫና ጋር ተያይዞ አሁንም ፍቱን አማራጭ እንዳልሆነ ያስረግጣል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት ለኢትዮጵያ በሰጠችው ብድር እና ድጋፍ ምትክ በሰጥቶ መቀበል ብሂል ልትጠይቃቸው በምትችላቸው ጉዳዮች ላይም አቶ ዘሪሁን መላምቶችን ያጋራል።
የምጣኔ ሃብት እና ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በወዳጅነት ብቻ የሚደረግ ምንም ነገር የለም የሚለው አቶ ዘሪሁን፣ "የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በአፍሪቃ ቀንድ ቀጠና እና በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ተደማጭነትን መፍጠር ትፈልጋለች፡፡ ተጽዕኖዋን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ያላት ፍላጎት ባለፉት ዓመታት ታይቷል፡፡" ይላል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይሄንን ብድር በምን ሁኔታ እንደወሰደ ዝርዝር ማብራሪያዎች ባይሰጡም በደግነት እንዳልሆነ ግን ያስረግጣል።
ኢትዮጵያ በጊዜያት ውስጥ የየተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቋም እንድትደግፍ ልትጠየቅ እንደምትችል ግምቱን ያስቀምጣል፡፡
በዳረጎትና በብድር እስከመቼ?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ በብድር እና ችሮታ ከገባችበት የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ለዘለቄታው መውጣት እንደማትችል ያስረግጣሉ፡፡
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ አሁን በሀገሪቱ የተጀመሩ አንዳንድ እርምጃዎች ቀስ በቀስ ሀገርን አትራፊ እንደሚያደርጉ ዕምነት አላቸው፡፡
ከእነዚህ ርምጃዎች በመንግሥት እጅ ሥር ያሉ ንግድ ተቋማት ወደ ግል ባለሀብቶች የማዘዋወር ጅማሬ አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
"ይሄ እርምጃ ለግንባታዎች የሚሆን በቂ ገንዘብ በማስገኘት፣ በራሳቸው በድርጅቶቹ ውስጥ የተሻለ ትርፋማነት እና የሥራ ውጤታማነት ያስገኛል" ሲሉ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡
አቶ ዘሪሁን በበኩሉ ኢትዮጵያ በነባር ዕዳ ላይ ዕዳን ከማከል ታቅባ የፖለቲካ ተሰሚነቷን በማሳደግ በተለያዩ የምዕራብ እና ሩቅ ምሥራቅ ሀገራት መዝገብ ላይ የሰፈረ ውዝፍ ዕዳዋን ለማሰረዝ ጥረት ብታደርግ ይመርጣል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእርሻ መሬት አላት። ወደ 72 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት አላት። ወንዞቻችን ወደ 122 ቢሊየን ኩዩቢክ ሊትር ዉሃ ይዘው ነው የሚወጡት። እኛ ይሄን ይዘን አርሰን ማምረት አልተሳካልንም። ቢሳካልን ኑሮ የገቢ ወጪ የንግድ ሚዛኑም ይስተካከል ነበር።"ይላሉ።
ከእነዚህ የመፍትሄ ሀሳቦች በተጨማሪ ግን ኢትዮጵያ በገፍ ከውጭ ሀገራት ሸቀጦችን ከማስገባት ድና ምርቶቿን በከፍተኛ መጠን ለሌሎች ሀገራት መሸጥ የምትጀምርበትን፣ የወጪ እና ገቢ ንግዶች የሚመጣጠኑበት መላ እንዲበጅ የኢኮኖሚ ልሂቃኑ ይመክራሉ፡፡
አነሰም በዛም ዕዳም ሆነ ችሮታ እንደየ ሁኔታው ወደ ዜጎች የሚሻገር የተዋረድ ጫና አለውና፡፡












