የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሼ ዞን አመራሮች በታጣቂዎች ተገደሉ

የካማሼ ዞን

የፎቶው ባለመብት, Google earth

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት 4 የካማሼ ዞን አመራሮች ሲገደሉ የተወሰኑ መቁሰላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነርን ጠቅሰው የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው አቶ በፍቃዱ አዳነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቤንሻንጉል ጉምዝና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ አመራር አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ መስከረም 15 በአሶሳ ላይ ስብሰባ አካሂደው ነበር።

ስብሰባውንም ጨርሰው የካማሼ ዞንና የአምስት ወረዳ አመራሮች በሚመለሱበት ወቅት በካማሼና ነዶ መካከል በምትገኝ ቦታ በተከፈተ ተኩስ አራት የካማሼ ዞን አመራሮች እንደተገደሉ አቶ በፍቃዱ ገልፀዋል።

አቶ በፍቃዱ ጥቃት አድራሾቹን ማንነት "ፀረ ሰላም ኃይሎች" ከማለት ውጭ ያሉት የለም።

ከአመራሮቹም በተጨማሪ የፀጥታ ኃይል አባላት በዚህ ተኩስ እንደቆሰሉ ገልፀው፤ በህይወት ያሉት የት እንዳሉ እንደማይታወቁ ና አቶ በፍቃዱ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰይፈዲን ሃሮን እንዳስታወቁ ገልፀዋል።

ሁኔታውን ለማረጋጋት የመከላከያ ኃይል ወደ ቦታው የገባ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።