ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ላይቤሪያ እንደታተመ ጠፋ ያለችው 60 ሚሊዮን ዶላር እያወዛገበ ነው
ላይቤሪያ በውጭ አገር ካሳተመቻቸው ገንዘቦች በአንድ ኮንቴነር የነበረና 60 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው ገንዘቧ የገባበት እንዳልታወቀ አስታውቃ ነበር።
በዚህም ተጠያቂ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ የአገሪቱ ባለስልጣናትና የባንክ ገዥዎች ከአገር እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
የቀድሞ የአገሪቱ ማእከላዊ ባንክ ገዥ ሚልተን ዊክስ በሚደረገው ምርመራ ፖሊስን ለመተባበር ዝግጁ እንደሆኑ ነገር ግን እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት ከታተመ በኋላ ጠፋ ስለተባለው የገንዘብ ኮንቴነር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"እኔ ራሴ ጠፋ ስለተባለው ገንዘብ ፣ እነዚህ ውንጀላዎች ከየት እንደመጡ ማወቅ እፈልጋለው" ብለዋል።
ቀደም ሲል የአገሪቱ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር እንዳስታወቀው 60 ሚሊዮን ዶላር ጠፋ ከመባሉ ጋር በተያያዘ ከአገር ውስጥ እንዳይወጡ ከታገዱ 15 ሰዎች መካከል የባንክ ገዥው ይገኙበታል።
የማእከላዊ ባንኩ ምክትል ገዥ የሆኑት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ልጅ ቻርልስ ሰርሊፍ ከታገዱት መካከል አንዱ ናቸው።
ኤለን ሰርሊፍ እስካሁን ጉዳዩን በሚመለከት ያሉት ነገር የለም።
መንግሥት ወደ አገሪቱ ማእከላዊ ባንክ መግባት ሲኖርበት በዚያው ጠፋ የተባለው ገንዘብን በሚመለከት ከፍተኛ ምርመራ እንደሚያደርግ ያስታወቀ ሲሆን ነገሩ የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችልም አመልክቷል።
የላይቤሪያ ዴይሊ ኦብዘርቨር ማእከላዊ ባንክ የጠፋ ገንዘብ የለም በማለት ነገሩን እንደካደ ዘግቧል።