ዛምቢያ የተቃዋሚ ፓርቲው ፓለቲከኛ የጥገኝነት ጥያቄ አስተባበለች

የዚምባብዌ ተቃዋሚ ኤምዲሲ ጥምረት ከፍተኛ አመራር ቴንዳይ ቢቲ ዛምቢያ ጥገኝነት ሊጠይቁ ነበር መባሉን አስተባበሉ።

የዚምባብዌ ፖሊስ ቴንዳይ ቢቲን ባለፈው ሳምንት የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ አለመረጋጋትና ግጭት እንዲሰፍን ቀስቅሰዋል ሲል ይወነጅላቸዋል።

የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆይ ማላንጂ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቴንዳይ ቢቲ ጥገኝነት ጠይቀዋል የሚለው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው።

ወደ ዚምባብዌ እስኪመለሱ ድረስ "ደህንነታቸው ተጠብቆ በጥበቃ ስር" ይቆያሉ ብለዋል ሚኒስትሩ።

ቀደም ብሎ የተቃዋሚው መሪ ቴንዳይ ቢቲ ጠበቃ ደንበኛቸው በዛምቢያ ድንበር ላይ በዚምባብዌ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረው ነበር።

የዛምቢያ ፖሊስ ሪፖርት ነው የተባለ ማስረጃ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ እየተዘዋወረ ሲሆን የዚምባብዌ ባለስልጣናት ቴንዳይ ቢቲ የዛምቢያ ድንበርን ካቋረጡ በኋላ በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው ሞክረው ነበር ይላል።

የተቃዋሚ ፖለቲከኛው የድረሱልኝ ጩኸት ካሰሙ በኋላ 300 የሚሆኑ ዚምባብዌያውያን የመንግስት የደህንነት ሰራተኞቹ በቁጥጥር ስር እንዳያውሏቸው ተከላክላለዋል ይላል ሪፖርቱ።

ከዛም በኋላ የዛምቢያ ባለስልጣናት ጣልቃ ገብተውና "በዛምቢያ ግዛት ውስጥ ይህንን ቢያደርጉ" የዚምባብዌ ሃላፊዎችን በቁጥጥር ስር እንደሚያውሏቸው ገልፀው እንዳስለቀቋቸው ተገልጿል።

የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለቢቢሲ እንደገለፁት የቴንዳይ ቢቲ የጥገኝነት ጠየቁ የሚለው "ተቀባይነት የሌለው " ነው።

ከሮበርት ሙጋቤ የ37 ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላ ባለፈው ወር የተደረገው ምርጫ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ ሀራሬ ተቃዋሚዎች ሊያደርጉት የነበረውን ሰልፍ ፖሊስ ለመከልከል ጣልቃ ከገባ በኋላ የስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች በፍርሃት የተነሳ መደበቃቸውን ዘጋቢዎች ገልፀዋል።

በምርጫው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ማሸነፋቸውን የምርጫ ኮሚሽኑ ቢያውጅም ኤምዲሲ የተሰኘው ጥምረት ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ሲል ክሱን ያሰማል።