ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሰልፉን ዘግቡ ብሎ ማስገደድ ይችላል?
ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የተደረገውን የድጋፍ ሰልፍ ተከትሎ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለኢኤንኤን እንዲሁም ለትግራይ ክልል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከሰልፉ ሽፋን ጋር በተያያዘ ደብዳቤ መፃፉ ላለፉት ሁለት ቀናት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
አንዳንዶች እንደገመቱት ባለሥልጣኑ ለተቋማቱ ደብዳቤ የፃፈው "ለምን ቀጥታ አላስተላለፋችሁም?" በሚል ሳይሆን በጊዜው ስለ ሰልፉ ምንም ባለማለታቸው እንደሆነ የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙነት አቶ ፍቃዱ ውበቴ ለቢቢሲ ገልፀዋል፤ "ይህን ለማድረግም ተቋሙ ሥልጣን አለው" ይላሉ።
ባለሥልጣኑ ለሕዝብ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም አስተዋፅኦ የሚያደርጉ መገናኛ ብዙኃን እንዲበራከቱ የሚሠራ መሆኑን በማስታወስ የመገናኛ ብዙኃንም በሃገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እየተከታተሉ ለሕዝቡ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለባቸው ባለሙያው ይናገራሉ።
ለመገናኛ ብዙኃኑ ፍቃድ ሲሰጥም እነዚህ ነገሮች ከግምት ገብተው እንደሆነም ያመለክታሉ።ከዚህ በመነሳት እንዲሁም ጉዳዩ ካለው ሕዝባዊ ጠቀሜታ አንፃር ተቋማቸው ለቴሌቭዥን ጣቢያዎቹ ደብዳቤ እንደፃፈና ይህን ለማድረግም ተቋሙ ሥልጣን እንዳለው ገልፀዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ ግን ባለሥልጣኑ ለሚዲያዎቹ ለምን የድጋፍ ሰልፉን አላስተላለፋችሁም ብሎ ማብራሪያ የመጠየቅ ሥልጣን እንደሌለው ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ይልቁንም የድጋፍ ሰልፉ ሰው የአገር ጉዳይ ነው ብሎ የሚሰማውና መገናኛ ብዙኃንም ፈጥነው ሊዘግቡ የሚረባረቡበት ዓይነት ነው።
"ባለማድረጋቸው ነውር ነው ሊባል ይችል ይሆናል።ነገር ግን ይህ የሕግ ግዴታ ያለበት ነገር አይደለም" ይላሉ።
የትግራይ ቴሌቭዥን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አባዲ በሕግ ባለሞያው አቶ አብዱ ሃሳብ ይስማማሉ።
"የሚተላለፉት ፕሮግራሞችን በሚመለከት ሕገ መንግሥቱን የሚጻረሩ፣ ሕዝብ ለሕዝብ የሚያጋጩና ሃይማኖት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጣረሱ ዝግጅቶች ከተላለፉ ባለሥልጣኑ የመጠየቅ ኃላፊነት አለው። ዝግጅቶች ከመተላለፋቸዉ በፊት ግን የትኛውን ፕሮግራም ነው የምታስተላልፈው፣ የትኛውን ነው ያላስተላለፍከው ብሎ ለመጠየቅ የሚፈቅድለት አዋጅ የለም" በማለት ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በተለይም ባለሥልጣኑ እንደ ኢኤንኤን ላለ የግል ሚዲያ በዚህ መልኩ ደብዳቤ መፃፍ አይችልም ሲሉ የሚያስረግጡት አቶ አብዱ ምናልባት ትግራይ ክልል ቴሌቭዥን የሕዝብ ነው ከሚል መነሻ ደብዳቤው ተፃፈ ቢባል እንኳ ይህም ራሱ አከራካሪ ነው ይላሉ።
የትግራይ ክልል ቴሌቭዥን እንደ ሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ከሕዝብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ግዴታ አለበት ቢባል እንኳ ይህ የሕዝብ አገልግሎት ነው አይደለም የሚል መከራከሪያ ሊኖር እንደሚችል አቶ አብዱ ያስረዳሉ።
"በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ቴሌቭዥኑ ሰልፉን በቀጥታ ስላስተላለፈው የትግራይ ክልል ቴሌቭዥን ባለማስተላለፉ ምን አጎደለ?" የሚል ነገርም ጥያቄ እንደሚነሳም ይጠቁማሉ።
ብሮድካስት ባለሥልጣን ለዓመታት ይህን አስተላልፋችኋል፤ ያን አላስተላለፋችሁም በማለት ባልተገባ መልኩ መገናኛ ብዙሃንን ሲጠይቅ መቆየቱን ያስታውሳሉ።
በመጨረሻም አቶ አብዱ "የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ኢትዮጵያን የሚመለከት ነገር ሳይዘግብ ሲቀር መቼ ነው የጠሩት።ኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ኢትዮጵያ ሬድዮ ለዓመታት ሲቀልዱ ብሮድካስት ባለሥልጣን የት ነበር?" በማለት ይጠይቃሉ።