ዲግሪ ከማግኘትም በፊት ራስን ማግኘት

እኛ ወጣቶች ዲግሪ እንድንጭን የበዛ ጫና ነው ያለብን። ያውም ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ

አውቃለሁ፤ ይህን ጉዳይ ኅብረተሰቡ እንደዋዛ ሊመለከተው እንደሚችል፤ እውነታው ግን ይኸው ነው።

ቤን እባላለሁ።ራሴን ለማጥፋት ስንት ጊዜ እንዳሰብኩ ብነግራችሁ አታምኑኝም።

ከልጅነቴ ጀምሮ ጭምት ነበርኩ። ዩኒቨርስቲ ስገባ ግን ነገሮቹ እየከፉ መጡ። ከሰው አልቀርብ፤ አልጫወት፥ አላጠና

ትዝ ይለኛል መጀመርያ የተመደብኩበት ዩኒቨርስቲ ስደርስ፤ በሕዝብ አውቶቡስ ነበር የሄድኩት። ሌሎች ዘናጭ ተማሪዎች ግን በወላጆቻቸው በልዩ ክብካቤ፤ እንደ እንቁላል ተይዘው፤ በውል ውል የግል አውቶሞቢል፤ መዓት ሻንጣዎቻቸው ተጭኖላቸው ነበር የመጡት።

እውነት ለመናገር የማየው ነገር ሁሉ እኔን ወደ መገለል ስሜት የሚከት ነበር።

ቢጤዎቼን ለመምሰል ሩቅ ነበርኩ፤ የኔ ቤተሰቦች ከሰራተኛው መደብ ናቸው።ከወላጆቼ የሚደረግልኝ ድጋፍ ምንም ነበር።

ኮርሶቼን መልክ አስይዞ በመረዳት ረገድ ነገሮች እንዳሰብኩት ቀላል አልሆኑልኝም። ሁሉም ነገር ለኔ ባዕድ ነበር።

ብዙዎቹ ተማሪዎች እገዛን ሲሹ የሚያማክሩት የሆነ የቅርብ ሰው ነበራቸው፡።እኔ ግን በአመዛኙ ባይተዋር ሆኜ ነው የቆየሁት።

አባቴ እንደሆነ ስለ ዩኒቨርስቲ ብዙም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም። ድሮ ነው ትምህርት አቋርጦ ወታደር ቤት የገባው።እናትና አባቴ የተለያዩት ደግሞ ገና የ16 ዓመት ወጣት ሳለሁ ነበር።

ከአባቴ ጋር ስኖር መልካም የሚባል ግንኙነት ነበረን ለማለት ይከብዳል።አንደኛ ሰካራም የሚባል ዓይነት ሰው ነው።

ከፍተኛ የመጠጥ ሱስ ነው ያለበት። በዚያ ላይ ሞገደኛ የሚባል ዓይነት ነው። ምንም ልንግባባ አልቻልንም።

መጀመርያ ዩኒቨርስቲ ስመደብ አባቴን ተገላገልኩት ብዬ ነበር። ⷎኖም ዩኒቨርስቲም የኔ የምለው ቦታ ሆኖ አላገኘሁትም። በፍፁም!

ገና ዶርም እንደገባሁ እርኩስ ሐሳቦች አእምሮዬን ጨምድደው መያዝ ጀመሩ። ገና እኮ 6 ወርም አልሆነኝም። የፍቅር ግንኙነትም ጀምሬ ነበር።

እንዲያ ከተባለ፤ እውነት ለመናገር ፍቅር ሳይሆን ጭቅጭቅና አለመግባባት የሞላው ነበር። ያን ሰሞን ትክክል አልነበርኩም። ስንለያይ ጊዜ ከአዲሱ ፍቅረኛዋ ጋር ተደባደብኩ።

በፍፁም ትክክል አልነበርኩም። ይባስ ብሎ አብዝቼ መጠጣትና ክላስ መቅጣት ጀመርኩ።

ሰካራምነቴ በመላው ዩኒቨርስቲ በመታወቁ የስነልቦና ባለሞያ እንድጎበኝ ተደረገ።ለእርዳታው ብዙም ዝግጁ አልነበርኩም። ለሚጠይቁኝ ጥያቄ ሁሉ አሉታዊ መልስ ነበር የምሰጣቸው።

ብቻ አንድ ሴሚስተር እንዲሁ አለፈ። አንድም ፈተና አላለፍኩም ብላችሁ አታምኑኝም።

ወደ ቤት መመለስ አሳፋሪ ነበር። ለአባቴ ምን ብዬ እንደምነግረው ግራ ገባኝ። ወደ ዩኒቨርስቲ እንደማልመለስ ሳልነግረው ሁለት ወራት አለፉ።

እሱም ለነገሩ በቀን በቀን ነው የሚሰክረው። እኔም ክፍሌ ውስጥ ቆልፌ ነበር አብዛኛውን ሰዓት የማሳልፈው። ድንገት አዲስ ሐሳብ ተከሰተልኝ።

እንዴት እስከዛሬ ሳላስበው ቀረሁ! ራስን ስለማጥፋት!

ቤት የነበረ መዓት መድኃኒት መዋጥ ጀመርኩ።ከአንድ ሰዓት በኋላ ግን ምንድነው እያደረኩ የነበረው ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። በአንቡላንስ ወደ ሆስፒታል ሄድኩኝ።

ምን ብዬ ነው ለሐኪሞቹ የምነግራቸው? ግራ ገባኝ። የሆነ ዓይነት ከባድ ቅጣት እንደሚጥሉብኝ ስለተሰማኝ ከፍተኛ የራስ ውዝግብ ውስጥ ገባሁ። አታምኑኝም፤ ተሳፍሬ ወደ ቤት ተመለስኩ።

ጭንቅላቴን ይደቃኛል።ነገሮች ድብልቅልቅ አሉብኝ። ደግነቱ አባቴ ቤት አልነበረም። ገብቼ ተኛሁ። ሆኖም ታመምኩ። ሌሊቱን ሙሉ እንዲሁ ታምሜ አደርኩ። እንደዚያም ሆኜ ስለሆነው ነገር ለማንም ትንፍሽ አላልኩም።

እንደነገርኳችሁ ጭምት ሰው ነበርኩ፡።

ለምን እንደሆን አላውቅም ከሌሎች ሰዎች እርዳታን መጠየቅ በፍርሃት የሚያንዘፈዝፈኝ ጉዳይ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። እርዳታን ብጠይቅ ኖሮ ምናልባት ነገሮች እንዲህ አይከፉም ነበር።

ራስን የማጥፋት ሐሳብ ሲፀናወት ነገሮችን በምክንያት አናስብም። የሆነ ግዙፍ እኩይ ስሜት እላያችሁ ላይ ይሰፍርና ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራችኋል።ለምሳሌ እኔ ከዚህ መንፈስ ለመላቀቅ ያልሞከርኩት ነገር፤ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ አልነበረም።

ወታደር ሆኖ ከመዝመት ጀምሮ ከባድ ወንጀል ሰርቶ በገዛ ፈቃድ እስር ቤት እስከመግባት ያለውን አማራጭ ሁሉ አስቤያለሁ።

በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ክረምቱ መጨረሻ ላይ ከዩኒቨርስቲዬ ደብዳቤ ደረሰኝ። የደብዳቤው ይዘት ሁሉንም ፈተና ስለወደቅኩ ወደ ዩኒቨርስቲው በር ድርሽ እንዳልል የሚያትት ነበር።

ስለሁኔታው አባቴን መንገር ነበረብኝ። እውነት ለመናገር አባዬ እንዲህ ዓይነት ነገር ለማውራት የሚመች ዓይነት ሰው አልነበረም። ሞገደኛ ነው ብያችሁ የለ!

እንደፈራሁት አልሆነም። ስነግረው ሥራ ፈልጌ ማግኘት እንዳለብኝ ነገረኘ።

ለአምስት ወራት እግሬ እስኪቀጥን ሥራ ፈለኩ። አልተሳካም። በድጋሚ ጥልቅ ድብታ ውስጥ ተዘፈቅኩ። ቤት ተዘፍዝፎ መዋል ሆነ ሥራዬ።

ማኅበረሰቡን በሙሉ ጠምጄ ያዝኩት። ሰው ጠላሁ። ራሴን ጠላሁ። አካባቢዬን ጠላሁ። ዓለምን ጥምድ አድርጌ ያዝኳት። እንደኔው ዓለም ጀርባዋን የሰጠችው ጓደኛ አገኘሁ።

ሁለታችንም በአገራችንና በኑሯችን የተሰላቸን ሰዎች ስለነበርን ለመግባባት ጊዜ አልወሰደብንም። ከአገር ለመሰደድ ወሰንን። ወደ ቡዳፔስት ጠፋን። ለአባቴ ግን ለሁለት ሳምንት ሽርሽር እየሄድኩ እንደሆነ ብቻ ነበር የነገርኩት። ለአንድ ዓመት አልተመለስኩም።

አባቴ ሲጨንቀው ለፖሊስ ሪፖርት አድርጎ ኖሮ ከፖሊስ ጣቢያ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። ደህና እንደሆንኩና ከአባቴ ጋር ለማውራት ግን በፍፁም ፍቃደኛ እንዳልሆንኩ ነግሪያቸው ስልኬን ዘጋሁት።

ወደ ቡዳቤስት የሄድነው እቅድ ኖሮን ሳይሆን በአቦሰጥ ነበር። ምን እንደምንሠራ እንኳ መረጃው አልነበረንም። ከቡዳፔስት ግሪክ፤ ከግሪክ ቱርክ፤ ከቱርክ የባልካን አገሮችን በሙሉ አዳረስን። ስፔንና ሞሮኮ ሁሉ አልቀሩንም።

ምግብ ከሰው ቤት እየለመንን፤ መጓጓዣ ከመኪና ኋላ እየተንጠላጠልን ነበር ከአገር አገር የምንሄደው። በርግጥ ጉዞው ከገባሁበት ጥልቅ ድብታ መንጭቆ ባያወጣኝም ራስን ስለማጥፋት የማስበውን ነገር ቀንሶልኝ ነበር።

አንደኛ ከኔ በባሰ አስቸጋሪ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች በሁሉም ሥፍራ እንደሚገኙ እንድረዳ አድርጎኛል፤ ሁለተኛ ደግሞ ከግል ፍርሃቴ ወጥቼ ከዓለም ጋር ለመጋፈጥ መንገድ ከፍቶልኛል።

ወደ አገሬ ስመለስ ነገሮች እንዲለወጡ በፅኑ ፍላጎት አሳድሬ ነበር። በተለይም ሥራ ለማግኘት ቁርጠኛ ነበርኩ።

ደግሞም ተሳካልኝ። 27 ዓመት ሲሞላኝ ሕይወቴ ቀስ በቀስ መልክ መያዝ ጀመረ። ሥራ አገኘሁ፤ ሚስት አገባሁ፤ ልጅ ወለድኩ።

ከቤተሰባችን ይሁን ከአስተዳደጌ አላውቅም ብቻ ችግሬን ወደ ውስጥ እንጂ ለሌሎች የማጋራት ነገር አላውቅም።

ማንኛውንም ጭንቀቴን በራሴው አፍኜ መቀመጤ በብዙ ጎድቶኛል። እንደኔው በብቸኝነት መቀመጤ ሳይጎዳኝ አልቀረም።

ለረዥም ጊዜ ያህል ከዩኒቨርስቲ መባረር የዓለም መጨረሻ እንደሆነ አስቤ ነበር። ልክ እንዳልነበረ ያወቅኩት ግን ዘግይቼ ነው።

ዋናው ነገር ራስን ተረድቶ የሰዎች እርዳታ በሚያስፈልግ ጊዜ ሁሉ ያን መሻት ነው። የዩኒቨርስቲ ዲግሪን መጫን የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑ መልካም ነገር አይመስለኝም። በዚህ ረገድ ማኅበረሰቡ የማይታይና የማይዳሰስ ጫናን ነው በወጣቶች ላይ የሚፈጥረው።

በኔ ሕይወት የተረዳሁት ግን ዲግሪን አናታችን ላይ ከመጫንም በፊት ጤናማ ጭንቅላት እንዲኖረን ማስፈለጉን ነው።