ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመቅደላ 150ኛ ዓመት
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የሞቱበትን 150ኛ ዓመት በልዩ ሁኔታ ለመዘከር ዝግጅት ላይ ነኝ እያለ ነው።
"የመቅደላ 150ኛ ዓመት" የሚል ስያሜ የተቸረው ዝክረ-በዓል ከሥነ-ትምህርታዊ እና ባህላዊ ዓላማዎቹ ባሻገር የክልሉን የቱሪዝም መዳረሻዎች የማስፋት ተጨማሪ ዓላማ ሰንቋል ተብሏል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ፤ በንጉሡ ታሪካዊ ሚና ላይ ጥናቶች ይከናወናሉ እንዲሁም ማስረጃዎች ይሰነዳሉ ብለዋል።
አፄ ቴዎድሮስ መድፍን ጨምሮ የልዩ ልዩ ዘመናዊ ቁሶች ማምረቻ ማዕከል ትሆን ዘንድ አጭተዋት የነበረችው የጋፋት እንዲሁም ህይወታቸው ያለፈችባት የመቅደላ አካባቢዎች የሚገባቸውን ትኩረት እንዲያገኙ ግፊት ይደረጋል ሲሉ ዶክተር ደሳለኝ ጨምረው ተናግረዋል።
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ወልደማርያም በበኩላቸው በመጭው ሚያዝያ የሚውለውን ዝክረ-በዓል ከመቅደላ ተዘርፈው ወደእንግሊዝ የተወሰዱ ቅርሶች እንዲመለሱ ተጨማሪ ጥሪ የሚቀርብበት ነው ብለዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረው የቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ የንጉሡን ሞት ተከትሎ ከመቅደላ አምባ የተዘረፉ ታሪካዊ፥ ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ ቅርሶች እንዲመለሱ ጉትጎታ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር ሒሩት፤ ሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው በዚህ ረገድ አሁንም ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን በደምሳሳው ተናግረዋል።
ዝከረ-በዓሉን የጎንደር ዩኒቨርስቲ ታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል የሚያስተባብረው ሲሆን ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር አብሮ በጥምረት እንደሚሰራ ተገልጿል።
የጎንደር ከተማ በቅርቡ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የተወለዱበትን 200ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሯ ይታወሳል።