ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካለሁበት 2፡ ''ከምንም በላይ እናቴን ማየት እፈልጋለሁ''
ደሳለኝ ጉደታ እባለለሁ። በአሜሪካን ሃገር አሪዞና ግዛት፤ ፊኒክስ በምትባል ከተማ ውስጥ ነው የምኖረው። ከአስር ዓመታት በፊት ነበር ዲቪ ደርሶኝ ወደ እዚህ ልመጣ የቻልኩት። ይህን ከተማ የመረጥኩት ቪዛ እንዳገኝ ድጋፍ ሲያደርግልኝ የነበረው ግለሰብ በዚህ ከተማ ይኖር ስለነበረ ነው።
የአሪዞና ግዛት ከሜክሲኮ ጋር ትዋሰናለች። እአአ 1848 ዓ.ም ድረስም የሜክሲኮ አካል ነበረች። በዚህም ምክንያት አሪዞና በርካታ ነገሮችን ከሜክሲኮ ጋር ትጋራለች። ምግባቸው ልክ እንደኛው ሃገር ቅመም የበዛበት ነው። ታኮስ እና ቡሪቶስ የተባሉ ምግቦችን መመገብ እወዳለሁ። እነዚህን ምግቦች ከእንጀራ ጋር ከሚመሳሰል ቡዴና በሚባል ነገር ነው የሚበላው።
አሪዞና በርሃማ ሥፍራ ነው፤ ብዙ አረንጓዴ ቦታን ማየት አይቻልም። ያደኩበት ሥፍራ ግን ለምለምና አረንጓዴ ነው። ከሚናፍቁኝ ነገሮች መካከልም አንዱ ይህ ነው። ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሲያትልና ሜሪላንድ ግን አረንጓዴ ናቸው። በዋሽንግተን ዲሲ እና በፊኒክስ መካከል የ3700 ኪ.ሜ እርቀት አለ። ይህም የኢትዮጵያ ቁመት ሁለት እጥፍ ማለት ነው። አሪዞና ተራራማ ቢሆንም ዛፎች ግን የሉትም።
አሪዞና በአሜሪካ ከሚገኙ ግዛቶች መካከል ሞቃታማው ነው። በደረቃማ ወቅት የሙቀቱ መጠን 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። በቴሌቪዥን ካልሆነ በስተቀር አሪዞና ውስጥ በርዶ አይቼ አላውቅም። የአየር ማቀዝቀዣ ዘዴዎች ባይኖሩ ኖሮ በዚህ መኖር የሚቻል አይመስለኝም።
በግዛቷ ውስጥ ጎብኚዎችን የሚስቡ በርካታ ተራሮች አሉ። ዝነኛው ግራንድ ካንዮን በአሪዞና ይገኛል እኔ ግን ወደዛ ሄጄ አላውቅም። ብዙ ጊዜ የሶስት ዓመት ልጄን ይዤ በአቅራቢያችን ወደሚገኘው ለልጆች ምቹ ወደሆነው መናፈሻ መሄድን እመርጣለው።
በዚህ ግዛት ውስጥ መኖርን ልዩ ከሚያደርገው ነገር መካከል መብቶቼ በሙሉ በህግ የተጠበቁ ናቸው ነው። ልክ እንደ ነጮቹ ሙሉ መብትና ነጻነት አለኝ። ይህ ደግሞ ለእኔ ትልቅ ጸጋ ነው።
ሰርቼ በማገኘው ገንዘብ በሃገር ቤት የሚገኙ ቤተሰቦቼን እረዳለሁ። ወደእዚህ ሃገር ባልመጣ ኖሮ ሃገር ውስጥ እየሰራሁ ቤተሰቦቼን መርዳት ሊከብደኝ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ወንድምና እህቶቼ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየረዳኋቸው ነው። ይህም በውስጤ ትልቅ ደስታን ይፈጥራል።
በቅርቡ በህክምናው ዘርፍ የላብራቶሪ ባለሙያ ለመሆን ትምህርቴን አጠናቅቄ እመረቃለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በአሪዞና መልካም ከሆኑልኝ ስኬቶቼ መካከል ትዳር መስርቼ የሴት ልጅ አባት መሆኔ ነው።
አሁን ሃገር ቤት ብሆን ብዙ ማስተካከል የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ። ብችል የአሪዞናን የአየር ጠባይ ብቀይር ደስ ይለኛል። በአሪዞና ከአስር ዓመታት በላይ ብኖርም እሰካሁን ድርስ ግን የአየር ጠባዩን መልመድ አልቻልኩም። ሌላው ደግሞ በአሜሪካ የጤና አገልግሎት እጅግ ውድ በመሆኑ ብችል የጤና አገልግሎቱን ነጻ ባደርገው ደስ ይለኝ ነበር።
ሁሌም እዚህ የሚኖሩ ሰዎች ሃሰተኞች (ፌክ) እንደሆኑ ይሰማኛል። ከሰዎች ጋር የለኝ ጓደኝነት የሃሰት እንደሆነ ይታወቀኛል። እውነተኛ ጓደኝነት ለጥቂት ጊዜ ነው የሚዘልቀው። ከማግባቴ በፊት ብቸኝነት ያጠቃኝ ነበር። ሃገሬ ኢትዮጵያ በሆን ኖሮ ይህ አይነት ስሜት አይሰማኝም ነበር። ሌላው ቀርቶ አብሮ አደግ ጓደኞቼ እዚህ ከመጡ በኋላ ይቀየራሉ። ማንም ስለሰው አይጨነቅም። ስላምታ እንኳን የለም።
ምናልባት የአኗኗር ዝይቤው ሊሆን ይችላል የሚቀይራቸው። አብዛኛዎቹ ሁለት ሥራ ነው የሚሰሩት፤ በተለይ ደግሞ ልጆች ካሏቸው የምትቀራቸውን ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አልያም ደግሞ በመተኛት ሊያሳልፉ ይችላሉ። ይህ ሳስብ ታዲያ የደኩበትን አይነት ማህብረሰብ እጅጉን እናፍቃለሁ።
እዚህ የገጠመኝ ትልቁ ችግር የቤተሰብ ናፍቆት ነው። ለረጅም ጊዜ አጠገቤ ማንም አልነበረም። ነገር ግን ትዳር መመስረቴና ልጅ መውለዴ የአሜሪካ ኑሮዬን መልካም አድርጎታል።
ወደ ትውልድ ስፍራዬ መመለስ እፈልጋለሁ። ተወልጄ ያደኩት ወለጋ ሻምቡ በምትባል ከተማ ውስጥ ነው። ወደዛ ከሄድኩ አምስት ዓመታት አልፈዋል። ከምንም በላይ ግን እናቴን ማየት ነው የምሻው።
ለአመዩ ኢታና እንደነገረው
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦