የሞዛምቢክ መንግሥት ተቋማት ድረ ገጾች በመረጃ ጠላፊዎች እጅ ወደቁ

የሞዛምቢክ መንግሥት የሚገለገልባቸው ድረ ገጾች በኮምፒውተር መረጃ ጠላፊዎች እጅ መግባታቸው ተገለጸ።
የአገሪቱ መንግሥት ያሳለፍነው ሰኞ ድረ ገጾቹ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት እንደቀለበሰ ቢያስታውቅም፤ የኮምፒውተር መረጃ ጠላፊዎቹ ግን ከ30 በላይ ድረ ገጾች በቁጥጥራቸው ሥር እንደዋሉ ተናግረዋል።
'የመኒ ሀከርስ' የተባለው የኮምፒውተር መረጃ ሰርሳሪዎች ቡድን የሞዛምቢክ መንግሥት ተቋማት ድረ ገጾችን መጥለፋቸውን ይፋ አድርገዋል።
የአገሪቱን የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጨምሮ የ34 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ድረ ገጾች "ሙሉ በሙሉ ሰብረን በእጃችን አስገብተናል" ብለዋል።
ብሔራዊ የአደጋ ዝግጅት ቢሮ፣ የመንገድ ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የውሃ ኤጀንሲዎች እና የየብስ ጉዞ ተቋም ዒላማ ከተደረጉት መሥሪያ ቤቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
የኮምፒውተር መረጃ ጠላፊዎቹ የጠየቁት ገንዘብ ካልተሰጣቸው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ያሉ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ለሕዝብ እንደሚያጋልጡም አስጠንቅቀዋል።
የሞዛምቢክ ብሔራዊ የኤሌክትሮኒክ ተቋም ዋና ኃላፊ ኤሚኖ ጀሲ፤ ምንም መረጃ እንዳልተሰረቀ ሰኞ እለት ተናግረዋል።
መንግሥት ተጨማሪ መረጃ ከሰሞኑ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።












