በሁለተኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የትኞቹ ተጫዋቾች ልቀው ታይተዋል?

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዋች የአምና አሸናፊዎቹ ማንቸስተር ሲቲዎች ሃደርስፊልድ ላይ 6 ግብ ያስቆጠሩበት፤ ብራይተኖች በድጋሚ አስገራሚ ድል ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ የተቀዳጁበትና ቼልሲ የለንደን ተቀናቃኛቸው አርሰናልን 3 ለ 2 ያሸነፉበት ሆኖ አልፏል።

በሌሎች ጨዋታዎች በነሃሴ ወር ምንም ግብ ማስቆጠር ያልቻለው የቶተንሃሙ ሃሪ ኬን አንድ ግብ ሲያስቆጥር፤ የኤቨርተኑ አዲስ ፈራሚ ሪቻርልሰን አሁንም ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል የትኞቹ በጋሬት ክሩክ ምርጥ 11 ውስጥ ገቡ?

ግብ ጠባቂ- ጆርዳን ፒክፎርድ

የሳውዝሃምፕተኑ አዲስ አጥቂ ዳኒ ኢንግስ ወደ ግብ የሰደዳትን ኳስ ያዳነበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነበር። የኤቨርተኑ ግብ ጠባቂ በሌላ አጋጣሚ ስህተት ሰርቶ የነበረ ቢሆንም፤ ወዲያውኑ ስህተቱን አስተካክሎ ኳሱን ግብ ከመሆን አድኖታል።

ተከላካዮች- ሼን ዳፊ፥ ስቲቭ ኩክ፤ ቤንጃሚን ሜንዲ

ሼን ዳፊ: ባለፈው ሳምንት የብራይተኑ አሰልጣኝ ቡድኑ በዋትፎርድ ሲሸነፍ ተጫዋቾቹን በእጅጉ የኮነነ ቢሆንም፤ በዚህ ሳምንት ማንቸስተርን ባሸነፉበት ጨዋታ ግን አስራ አንዱም ተጫዋቾች ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተዋል ብሏል። ብዙ ሙገሳ ካገኙት ተጫዋቾች መካከል ደግሞ ተከላካዩ ሼን ዳፊ አንዱ ነበር። ሼን የማንቸስተር የፊት መስመር ተጫዋቾችን ፋታ ነስቷቸው ነበር።

ስቲቭ ኩክ: የበርንማውዙ የመሃል ተከላካይ ስቲቭ ቡድኑ ገና ወደ ፕሪምር ሊጉ ሳይቀላቀል ጀምሮ በታማኝነት ሲያገለግል የነበረ ተጫዋች ነው። ከዌስትሃም ጋር በነበራቸውም ጨዋታ ወጥ የሆነ አቋሙን ማሳየት ችሏል።

ቤንጃሚን ሜንዲ: የቤንጃሚን ሜንዲ በሲቲ ቤት ወደ ቋሚ አሰላለፍ መመለስ ከማንም በላይ የጠቀመው ለአጥቂው ሰርጂዮ አጉዌሮ ነው። ምክንያቱም ሜንዲ ጉልበቱንና ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደፊት በመውጣት የሚያሻማቸው ኳሶች ለአጉዌሮ ብዙ የግብ እድሎችን እየፈጠሩለት ነው።

ሃደርስፊልድ ላይ 6 ግብ ባስቆጠሩበት ጨዋታም ይህንኑ ነው ማድረግ የቻለው።

አማካዮች- ጊልፊ ሲጉድሰን፤ ዳቪድ ሲልቫ፤ ጄምስ ማዲሰን፤ ማርኮስ አሎንሶ

ጊልፊ ሲጉድሰን: ይህ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዘመን ብዙ ገንዘብ ወጥቶተበት ወደ ኤቨርተን ቢዘዋወርም፤ አስደሳች ጊዜ አላሳለፈም ነበር። በዚህ ዓመት ግን በአዲሱ አሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ ስር ሆኖ ድንቅ ብቃቱን የሚያሳየን ይመስላል።

አይስላንዳዊው ሲጉድሰን ከሳውዝሃምፕተን በነበራቸው ጨዋታ አስገራሚ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሎ ነበር።

ዳቪድ ሲልቫ: ሲቲዎች ሃደርስፊልድን ስድስት ለምንም በረመረሙበት ጨዋታ ዳቪድ ሲልቫ የቡድኑን ጨዋታ ሲያቀጣጥልና የመሃሉን ስፍራ በተገቢ ሁኔታ ሲመራ ነበር።

ማንቸስተር ዩናይትዶች በብራይተን ከተሸነፉ በኋላ ሲቲዎች ሊያቆሟቸው የሚችሉት ሊቨርፑሎች ብቻ ይመስላሉ።

ጄምስ ማዲሰን: ብራይተኖች በቻምፒዮንሺፑ በነበሩባቸው ጨዋታዎች ብዙም ብቃቱን ማሳየት ያልቻለው ማዲሰን ማንቸስተር ዩናይትድን ባሸነፉበት ጨዋታ ግን አስገራሚ ነበር።

ይህ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ባለፈው ሳምንት ዎልቭስ ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፤ አመቱ ጥሩ የሚሆንለት ይመስላል።

ማርኮስ አሎንሶ: የቼልሲው አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ ከአንቶኒዮ ኮንቴ ለየት ያለ አዲስ አይነት ቡድን ይዘው የመጡ ይመስላል። ይህ አጨዋወት ከተስማማቸው ተጫዋቾች መካከል ደግሞ አሎንሶ አንዱ ነው። በነጻነት እተጫወተ ነው። የማሸነፊያዋን ሶስተኛ ግብም ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂዎች- ካሉም ዊለሰን፤ ሰርጂዮ አጉዌሮ፤ ሃሪ ኬን

ካሉም ዊለሰን: የቦርንማውዙ ዊልሰን ቡድኑ ከዌስትሃም ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች እስካሁን አምስት ጊዜ ግብ አስቆጥሯል። በቅዳሜው ጨዋታም ሶስት የዌስትሃም ተጫዋቾችን አልፎ ያስቆጠራት ግብ ብቃቱን የምታሳይ ነች።

ሰርጂዮ አጉዌሮ: አርጀንቲናዊው አጥቂ ወደ አስፈሪ አቋሙ የተመለሰ ይመስላል። ሃደርስፊልድን ስድስት ለአንድ ሲያሸንፉ፤ ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ሃትሪክ መስራት ችሏል።

ከአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ጋርም ቢሆን ግንኙነታቸው የሰመረ ይመስላል። ተቀይሮ ሲወጣም አሰልጣኙ ደስታውን በመሳም ገልጾለታል።

ሃሪ ኬን: ሃሪ ኬን በመጨረሻም በነሃሴ ወር ያጋጠመውን የጎል ድርቅ መስበር ችሏል። እንደውም ያባከናቸው ሌሎች ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎች ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ ሃትሪክ መስራት ይችል ነበር።