ሩሲያ ለፊንላንድ ታቀርበው የነበረውን የጋዝ ምርት አቋረጠች

ነዳጅ ማስተላለፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ ወደ ፊንላንድ ትልክ የነበረውን የጋዝ ምርት ማቋረጧን አስታውቃለች።

ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የያዘችው ግብግብ የኃይል አቅርቦት ማቋረጥን በዋነኛነት ያማከለ ነው።

የአገሪቱ ግዙፍ የጋዝ አምራች ጋዝፕሮም ወደ ፊንላንድ ይላክ የነበረው ጋዝ የሚቆምበትን ሰዓት አሳውቋል።

ከዚያም አቅርቦቱ እንደተቋረጠ ፊንላንድ አረጋግጣለች።

ፊንላንድ ዜጎቼ የአቅርቦት እጥረት አይገጥማቸውም ብላለች።

ፊንላንድ ለሚቀብላት ጋዝ በሩሲያ ገንዘብ (ሩብልስ) ክፍያ እንድትፈጽም ብትጠየቅም አሻፈረኝ ማለቷ ይታወሳል።

የጋዝ አቅርቦቱ የተቋረጠው ከመገበያያ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም።

ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል ማመልከቻ እንደምታስገባ ማስታወቋ ሩሲያን አስቆጥቷል።

ሩሲያ የብዙ የአውሮፓ አገራት ጋዝ አቅራቢ ናት።

ምዕራባውያኑ ዩክሬን ውስጥ ሩሲያ በከፈተችው ጦርነት ማዕቀብ ሲጥሉባት፣ በምላሹ ለጋዝ አቅርቦት በሩብልስ ክፈሉ ብላለች።

የአውሮፓ ኅብረት ሩሲያ "እጅ ለመጠምዘዝ" እየሞከረች ነው ቢልም፣ ሩሲያ ማዕቀብ የጣሉባትን አገራት "ወዳጆቼ ያልሆኑ" በማለት ገልጻቸዋለች።

ሩሲያ ጋዝ ታቀርብላቸው የነበሩ አገራት በጦርነቱ ሳቢያ በተከሰተው የአቅርቦት መስተጓጎል የኑሮ ውድነት ገጥሟቸዋል።

ፊንላንድ አብዛኛውን ጋዝ የምታስገባው ከሩሲያ ቢሆንም፣ ይህ ግን ከአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ከ10 በመቶ በታች ነው የሚሸፍነው።

የፊንላንድ መንግሥት የሚያስተዳድረው ጋዝግሪድ ፊንላንድ እንዳለው፣ ኢማትራ በተባለ ጋዝ ማስተላለፊያ ይገባ የነበረው ጋዝ ተቋርጧል።

አሁን ላይ ለፊንላንድ የሚያስፈልገው ያህል ጋዝ እንዳለም ገልጿል።

ሌላው የፊንላንድ መንግሥት የሚያስተዳድረው ጋዝ አቅራቢ ጋሱም፣ ሩሲያ "በውሳኔዋ ትጸጸታለች" ብሏል።

አቅርቦት ሊቋረጥ እንደሚችል አስቀድመው በመገመታቸው በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ተቋሙ አስታውቋል።

የሩሲያ ቃል አቀባይ የጋዝ አቅርቦት ስለማቋረጥ ውሳኔው ተጠይቀው "ማንም ቢሆን ያሻውን ነገር በነጻ አያገኝም" ብለዋል።

ሩሲያ ባለፈው ሳምንት የፊንላንድን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማቋረጧ አይዘነጋም።