የጉግል መተርጎሚያ በትግርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች አገልግሎት ጀመረ

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል ትግርኛና ኦሮምኛን ጨምሮ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚናገራቸውን 24 አዳዲስ ቋንቋዎች በጉግል መተርጎሚያ ዝርዝሩ ውስጥ አካቷቸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ አስሩ ቋንቋዎች በአፍሪካ የሚነገሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኦሮምኛ ፣ ትግርኛ፣ ትዊ፣ ባምባራ፣ ክሪዎ፣ ሉጋንዳ ይገኙበታል።

በኢትዮጵያ እና በኬንያ ወደ 37 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ኦሮምኛን የሚናገሩ ሲሆን ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኤርትራና የትግራይ ተወላጆች ትግርኛን ይናገራሉ።

"ለዓመታት ጉግል መተርጎሚያ የቋንቋ ልዩነቶችን በማጥበብ በመላው ዓለም የሚገኙ ማህበረሰቦችን ለማገናኘት ረድቷል" ሲል የአሜሪካው ኩባንያ ገልጿል።

አክሎም አሁን ቋንቋቸው በአብዛኛው ቴክኖሎጂ ውክልና ያልተሰጣቸው ሰዎችን መርዳት ይፈልጋል ብሏል።

ከአዲሶቹ ቋንቋዎች መካከል በሰሜን ህንድ፣ ኔፓል እና ፊጂ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ ተናጋሪዎች ያሉት ቦጅፑሪ እንዲሁም በማልዴቪስ 300 ሺህ ህዝብ ተናጋሪ ያለው ድሂቨሪ ይገኙበታል።

አሁን የተካተቱትን ቋንቋዎች ጨምሮ በጉግል ተርጓሚ የተካተቱ አጠቃላይ ቋንቋዎች ብዛት ወደ 133 ደርሷል።

አዲሶቹ የተካተቱት ቋንቋዎች የቴክኖሎጂ ምዕራፍን እንደሚወክሉ ገልጾም ምሳሌ ሳይኖር የሚተረጉም የማሽን መማሪያ ሞዴል እንደሚጠቀሙ አስፍሯል።

ይህ ኮምፒውተርን ለማሰልጠንና ትርጉሞቹን በማሰባሰብ የመረጃ ቋቱን ለማካበት የሚያገለግሉ በርካታ ሰዎች ለሌሏቸው ቋንቋዎች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብሏል።

ነገር ግን ኩባንያው ቴክኖሎጂው ፍጹም እንዳልሆነ አምኗል።

ስለዚህ ትርጉሞቹ ትክክል ይሆናሉ? የሚል ጥያቄ የተነሳ ቢሆንም ቀደም ሲል ባሉት ቋንቋዎች ላይ ችግሮች እንዳሉ ተስተውለዋል።

" በበርካቶች የሚደገፉ ቋንቋዎች እኛ ጭምር የምንደግፋቸው በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ትላልቅ ቋንቋዎች እንደ ዮሩባ፣ ኢግቦ፣ ትርጉሙ በጣም ጥሩ የሚባል አይደለም። በእርግጠኝነት ማለት የሚቻለው ትርጉሙ ሀሳቡን ያስተላልፋል፤ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የቋንቋውን ረቂቅነት እንዲሁም ውስብስብነት ያጣል" በማለት የጉግል ትራንስሌት ተመራማሪ ሳይንቲስት አይዛክ ካስዌል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአዲሶቹ ቋንቋዎችም ከዚህ የተለየ ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ ቢሆንም እነዚህን ቋንቋዎች ለመጨመር ጥናት ያደረጉ ግለሰቦች ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"በመጨረሻም መወሰን ነበረብን እና ካነጋገርኳቸው ሰዎች የተረዳሁት ጉዳይ ቢኖር ለነሱ በጣም አዎንታዊ እንደሆነ ነው" ብለዋል አይዛክ ካስዌል።