በዒድ ሶላት ላይ ሁከት ፈጥረዋል የተባሉ 76 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ በኢድ ሶላት ላይ ረብሻ ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

የፎቶው ባለመብት, EthioTube

የምስሉ መግለጫ, በአዲስ አበባ በኢድ ሶላት ረብሻ ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ሚያዝያ 24/2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባው የዒድ ሰላት ላይ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር በግንባር ቀደምነት የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ።

ግብረ ኃይሉ ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ "የሁከትና ብጥብጥ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ለብጥብጥ መነሻ በማይሆን ምክንያት" ከስታዲየም ውጭ በተለምዶ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም አጠገብ ሆነው ባስነሱት ረብሻና ብጥብጥ በጸጥታ ኃይሎችና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጿል።

በፀጥታ አካላት ላይ ከደረሰው የአካል ጉዳት በተጨማሪ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይም ጉዳት መድረሱ ተጠቅሷል።

በበዓሉ ታዳሚዎች ላይ ግን የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት እንዳልደረሰ ተገልጿል።

ሁከትና ግርግሩ የተፈጠረው ስግደት እንደተጀመረ እንደሆነ፣ የፀጥታና ደኅንነት ግብረ ሀይሉ መንስኤውን እያጣራ እንደሚገኝና ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

"አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በቀልና ጥላቻን ቋጥረው እንዲሁም ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ስውር ተልዕኮ ወስደው" እንደነበር ጠቅሶ ይህም ለሁከቱ መነሻ እንደሆነ ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

እነዚህ ቡድኖች በአንዳንድ አካባቢዎች "ስለታማ ነገሮችን፣ የውጭ አገር አክራሪዎችን አርማና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎችን" ይዘው ወደ በዓሉ ስፍራ መሄዳቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

ከዚህ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው ባሻገር፣ በቀጣይም ጉዳዩን በማጣራት ሌሎች የድርጊቱ ተሳታፊዎችን "አድኖ በመያዝ ለሕግ እንደሚያቀርብ" ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የዓይን እማኞች ምን አሉ?

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀጥታ የተላለፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፖሊስ ድንጋይ ሲወረውሩ ወደነበሩ ሰዎች አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ አሳይተዋል።

በቀጥታ የተላለፉት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወደ ፀጥታ ኃይሎች እና ሕንጻዎች ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩ ሰዎችን ለማስቆም ሲከላከሉ የነበሩ ሰዎችንም አሳይተዋል።

ለኢድ ሶላት በወጡ ሰዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት እንዲከሰት ያደረገው ክስተት እስካሁን ግልጽ ባይሆንም፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ግን ቀደም ብሎ ሴት ሙስሊሞች ሲሰግዱ ከነበረበት አቅጣጫ የጥይት ወይም የአስለቃሽ ጭስ ሲተኮስ መስማታቸውን ተናግረዋል።

በቀጥታ በተላለፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ከአዲስ አበባ ስታዲየም አቅራቢያ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚያም መስተወቶች በሚወረወሩ ድንጋዮች ሲረግፉ ታይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ረብሻው በተፈጠረበት አካባቢ የመንገድ አካፋይ ላይ በተተከሉ የአበባ መትከያዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ለሶላት የወጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Fana BC

ቢቢሲ ያነጋገረውና ከቤተሰብ አባላቱ ጋር የኢድ ሶላት ለመስገድ ወደ ስታዲየም ያቀናው መሐመድ በተፈጠረው ግርግር ምክንያት የሶላት ሥነ ሥርዓቱ ሳይጠናቀቅ ምዕመኑ መበተኑን ተናግሯል።

በሰገዳ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ ሕዝብ እንደነበር የሚናገረው መሐመድ፤ "እኔና ቤተሰቤ ለሶላት የቆምነው በጨርቆስ አቅጣጫ ነበር" ይላል።

መሐመድ ሰገዳው ከመጀመሩ በፊት " ችግር ሊከሰት ስለሚችል ተጠንቅቃችሁ ስገዱ" የሚል የጥንቃቄ መልዕክት ከተላለፈ በኋላ የሶላት ሥነ ሥርዓቱን እንደጀመሩ ይናገራል።

ይሁን እንጂ በመስገድ ላይ ሳሉ የጥይት ይሁን የአስለቃሽ ጭስ ተኩስ በውል ያልለየው ድምጽ ከወደ መስቀል አደባባይ አቅጣጫ ደጋግሞ ይሰማ እንደነበር ተናግሯል።

"ሴቶች ከሚሰግዱበት አቅጣጫ ግርግርና ሩጫ ተመለከትን። ሶላት አቋርጠው የሚወጡ በርካታ ሰዎችን ተመለከትን፤ እኛም ልጆች ስለያዝን መረጋገጥ እንዳይኖር ብለን ሶላቱ ሳይጠናቀቅ ወደ ኋላ ሸሸን" ይላል።

ረብሻው በተቀሰቀሰበት ቦታ ነበርኩ የሚለው ሳዳም የተባለ ሌላኛው የዓይን እማኝ፤ ረብሻው የተቀሰቀሰው ለመስገድ በአንድ ቦታ ተሰባስበው የነረበሩ ሴቶች ከአካባቢው እንዲነሱ በፖሊስ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው ይላል።

ፌደራል ፖሊስ ሴቶቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ከተኮሰ በኋላ ወንዶች መጥተው ደንጋይ ወደ ፖሊስ አባላቱ መወርወር ጀመሩ ሲል ሳዳም ያየውን ለቢቢሲ ገልጿል።

ይህ የዓይን እማኝ ግርግሩን ተከትሎ ተረጋግጠው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን መመልከቱን ጨምሮ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ግርግሩን ተከትሎ ከወላጆች ጋር የተነጣጠሉ በርካታ ሕጻናት በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ በአካባቢው ባሉ መስጅዶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች ሆነው ወላጆቻቸውን እየተጠባበቁ እንደሆነ የማሕበራዊ ሚዲያ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

line

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጎንደር ከተማ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ሕዝበ ሙስሊሙን አስቆጥቶ ነበር።

በጎንደሩ ግጭት ከ20 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታውቆ ነበር።

ከከጎንደሩ ክስተት በኋላ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የእምነት ተቋማት ላይ ውድመት ደርሶ ነበር።

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ.ም. በደባርቅ ከተማ ሁለት መስጅዶች እንደተቃጠሉ የገለጸ ሲሆን የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ደግሞ በስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ በተመሳሳይ ቀን ሚያዝያ 20 ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች ላይ ውድመት እንደደረሰ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።