በአዲስ አበባው ግርግር ከ10 ወር ሕጻን ጀምሮ የጠፉ ልጆችን እያገናኙ ያሉት ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, FB
ዛሬ ሚያዝያ 24/2014 ዓ. ም. በአዲስ አበባ የዒድ ሶላት ላይ በተከሰተው ግርግር ሳቢያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተጠፋፉ ልጆችን ለማገናኘት ወጣቶች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ውለዋል።
የጠፉትን ልጆች ፎቶ እና የሚገኙነትን ቦታ በፌስቡክ ገጽ ላይ በማጋራት፣ ከ100 በላይ ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር እንዳገናኙ ወጣቶቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የቤተሰቦችን ስልክ ቁጥር እንዲሁም ጠፍተው የተገኙ ልጆችን ስም ዝርዝር በፌስቡክ እና በትዊተር ላይም ወጣቶቹ ሲያጋሩ ውለዋል።
ልጆቹ በተባረክ መስጊድ (በተለምዶ ሜክሲኮ ጀርመን መስጊድ)፣ በፍልውሃ መስጊድ እና በደንበል ፖሊስ ጣቢያም እንዲቆዩ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ፣ የኢድ ሶላት ከመሰገዱ በፊት በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም አካባቢ "ጥቂት ግለሰቦች ባስነሱት ረብሻ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል" ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፖሊስ ድንጋይ ሲወረውሩ ወደነበሩ ሰዎች አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ አሳይተዋል።
ወደ ጸጥታ ኃይሎች እና ሕንጻዎች ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩ ሰዎችን ለማስቆም ሲከላከሉ የነበሩ ሰዎችም ታይተዋል።
ለዒድ ሶላት በወጡ ሰዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት እንዲከሰት ያደረገው ክስተት እስካሁን ግልጽ ባይሆንም፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ግን ረፋድ ላይ ሴት ሙስሊሞች ሲሰግዱ ከነበረበት አቅጣጫ ጥይት ወይም አስለቃሽ ጭስ ሲተኮስ መስማታቸውን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, FB
"በዓልን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ማሳለፋችን ያሳዝናል"
አንዋር ናስር በፍልውሃ መስጊድ እና በተባረክ መስጊድ ወላጆችና ልጆችን ሲያገናኝ ነው የዋለው።
ከ120 እስከ 150 የሚደርሱ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳገናኘ ለቢቢሲ ገልጿል።
ረፋድ ላይ የዒድ ሶላት እየሰገዱ ሳለ ድንገት ሰዎች ሲሮጡ እና ሲያለቅሱ ያየው አንዋር፣ ግርግሩ ከተነሳ በኋላ በአቅራቢያው ከነበሩ ወጣቶች ጋር በመተባበር የጠፉ ልጆችን ወደ መስጊድ እንደወሰዱ ይናገራል።
"መንገድ ላይ የሚታየው ሰው ሁሉ ያለቅሳል፣ ሴቶች ያለቅሳሉ፣ አባቶች ያለቅሳሉ፣ እንዲያውም አብዛኛው ሰው እያለቀሰ ነበር. . . በቃ ለቅሶ ቤት በለው። በአካባቢው በአስለቃሽ ጭስ ተጎድተው የነበሩ ሴቶችም ነበሩ" ሲል ክስተቱን ገልጿል።
በግርግሩ የተጠፋፉ እናትና ልጅ፣ አባትና ልጅ ወደ ተባረክ መስጊድ እና ፍልውሃ መስጊድ እንዲሄዱ ካደረጉ በኋላ ጠፍተው ከነበሩት ልጆች አብዛኞቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደተገናኙ ገልጿል።
"ልጆቻቸውን ሲያጡ እንደሞቱባቸው ነበር እዬዬ ሲሉ የነበረው። ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያገኙ የነበረውን ስሜት ለመግለጽ ይከብዳል. . . ይሄኮ ጠፍቶ የነበረ እቃ ማግኘት አይደለም። ልጆች ናቸው፣ እና የቤተሰቦችን ደስታና እፎይታ መግለጽ ከባድ ነው።"
ከልጆች በተጨማሪ የጠፉ አዛውንቶችና ሕመምተኞችም እንደነበሩ አንዋር ተናግሯል።
በዓልን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ማሳለፍ እንደሚያሳዝን ገልጾ፣ "ምንዳውን ከሰው ሳይሆን ከፈጣሪ እናገኛለን" ሲል ስሜቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, FB
"የ10 ወር ሕጻን ጠፍቶ መገኘቱን ሰምተናል"
በተባረክ መስጊድ ወላጆችና ልጆችን በማገናኘት ሲያስተባብሩ ከነበሩት ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነ ስሙን የማንጠቅሰው ወጣት፣ በግርግሩ ወቅት የ10 ወር ሕጻን ጠፍቶ ደንበል ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ መስማታቸውን ገልጿል።
"እናትየዋ ደንግጣ ሌላ ሴት ነች ፖሊስ ጣቢያ ይዛ የሄደቸው። መረጃውን ያገኘነው መጅሊስ ከሚሠራ ሰው ነው። ልጁ እስካሁን ከቤተሰቦቹ ጋር መገናኘቱን አላወቅንም" ሲል አብራርቷል።
የአንድ ዓመት ተኩልና የሁለት ዓመት ልጅ ጠፍተው ማግኘታቸውንም ለቢቢሲ ገልጿል።
በግርግሩ በአስለቃሽ ጭስ የተጎዱ ሴቶች እንዲሁም ነፍሰ ጡር እናቶችም ወደ ሆስፒታል እንዲወሰዱ ሲያመቻቹም ነበር።
"የጠፉት ወላጆች ሕመም የኛም ሕመም ነው ብለን ነው ማገናኘት የጀመርነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያገኙ በደስታ ሲፈነድቁ ነበር። ነገ ከፈጣሪያችን የምናገኘውን ምንዳ በመከጀል ነው ይህን ያደረግነው" ብሏል ወጣቱ።
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገረው ወጣት፣ ስሜ ይቅር ብሎ "እኔም ልጆቼ ጠፍተው ተገኝተዋል። ልጆቻቸውን ሲያገኙ የሚጮሁ ቤተሰቦች ነበሩ. . . ምን ብዬ ልንገርህ? አንዳንዶቹ ያመሰግኑናል። አንዳንዶቹ እያለቀሱ ይሄዳሉ" ሲል ተናግሯል።
ልጆችና ቤተሰቦቻቸውን ከሚያገናኙ ወጣቶች አንዱ የሆነው ይህ ወጣት፣ ከ100 በላይ የጠፉ ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር ማገናኘታቸውን ገልጿል።
የወላጆቻቸውን ስልክ ቁጥር የማያውቁ ልጆች፣ በፍርሃት ያለቅሱ የነበሩ ልጆችም ነበሩ።
ወጣቶቹ ለልጆቹ ምግብና ውሃ አቅርበው ከቤተሰቦቻቸው እስከሚገናኙ ከለላ ሰጥተዋቸዋል።
ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው በማገናኘት ሂደቱ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውጭ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችም እንዳገዟቸው ወጣቶቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
" የዚህ ሰፈር ልጆች ይመስሉኛል። አላውቃቸውም ግን የሌላ እምነት ተከታዮች እዚህ መጥተው ሲረዱን ነበረ። እያገዙን ነበር። በተለይ አንድ ወጣት ደብረወርቅ ሕንጻ ጋ መኪና ላይ ቆሞ ሲያስተባብር ነው የዋለው።"
ከወጣቶቹ አንዱ ልጆችን ከወላጆቻቸው ማገናኘት የፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ገልጿል።
". . . ልጅ ጠፍቶ ሲገኝ ያለውን ስሜት ልጅ ያለው ሰው ያውቀዋል። ሕጻናትን ከቤተሰብ ስታገናኝ ትልቅ እርካታ ነው የምታገኘው። እኛ ይህንን የምናደርገው ለሌላ ሳይሆን እምነታችንም መልካም ማድረግን ስለሚያዝ ነው። ይኸው ነው።"

የፎቶው ባለመብት, FB












