በአዲስ አበባ የኢድ ሶላት ላይ ረብሻ መከሰቱን ፖሊስ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EthioTube
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ሚያዝያ 24/2014 ዓ.ም. የኢድ ሶላት ላይ በተከሰተ ረብሻ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታወቀ።
የመዲናዋ ፖሊስ የኢድ ሶላት ከመሰገዱ በፊት በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም አካባቢ "ጥቂት ግለሰቦች ባስነሱት ረብሻ በንብረት ላይ ጉዳት" ደርሷል ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀጥታ የተላለፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፖሊስ ድንጋይ ሲወረውሩ ወደነበሩ ሰዎች አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ አሳይተዋል።
በቀጥታ የተላለፉት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወደ ፀጥታ ኃይሎች እና ሕንጻዎች ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩ ሰዎችን ለማስቆም ሲከላከሉ የነበሩ ሰዎችንም አሳይተዋል።
ለኢድ ሶላት በወጡ ሰዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት እንዲከሰት ያደረገው ክስተት እስካሁን ግልጽ ባይሆንም፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ግን ቀደም ብሎ ሴት ሙስሊሞች ሲሰግዱ ከነበረበት አቅጣጫ የጥይት ወይም የአስለቃሽ ጭስ ሲተኮስ መስማታቸውን ተናግረዋል።
በቀጥታ በተላለፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ከአዲስ አበባ ስታዲየም አቅራቢያ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚያም መስተወቶች በሚወረወሩ ድንጋዮች ሲረግፉ ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ረብሻው በተፈጠረበት አካባቢ የመንገድ አካፋይ ላይ በተተከሉ የአበባ መትከያዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
ይህንን ክስተት ተከትሎ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ላይም ሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት ያሉት ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, Fana BC
ቢቢሲ ያነጋገረውና ከቤተሰብ አባላቱ ጋር የኢድ ሶላት ለመስገድ ወደ ስታዲየም ያቀናው መሐመድ በተፈጠረው ግርግር ምክንያት የሶላት ሥነ ሥርዓቱ ሳይጠናቀቅ ምዕመኑ መበተኑን ተናግሯል።
በሰገዳ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ ሕዝብ እንደነበር የሚናገረው መሐመድ፤ "እኔና ቤተሰቤ ለሶላት የቆምነው በጨርቆስ አቅጣጫ ነበር" ይላል።
መሐመድ ሰገዳው ከመጀመሩ በፊት " ችግር ሊከሰት ስለሚችል ተጠንቅቃችሁ ስገዱ" የሚል የጥንቃቄ መልዕክት ከተላለፈ በኋላ የሶላት ሥነ ሥርዓቱን እንደጀመሩ ይናገራል።
ይሁን እንጂ በመስገድ ላይ ሳሉ የጥይት ይሁን የአስለቃሽ ጭስ ተኩስ በውል ያልለየው ድምጽ ከወደ መስቀል አደባባይ አቅጣጫ ደጋግሞ ይሰማ እንደነበር ተናግሯል።
"ሴቶች ከሚሰግዱበት አቅጣጫ ግርግርና ሩጫ ተመለከትን። ሶላት አቋርጠው የሚወጡ በርካታ ሰዎችን ተመለከትን፤ እኛም ልጆች ስለያዝን መረጋገጥ እንዳይኖር ብለን ሶላቱ ሳይጠናቀቅ ወደ ኋላ ሸሸን" ይላል።
ረብሻው በተቀሰቀሰበት ቦታ ነበርኩ የሚለው ሳዳም የተባለ ሌላኛው የዓይን እማኝ፤ ረብሻው የተቀሰቀሰው ለመስገድ በአንድ ቦታ ተሰባስበው የነረበሩ ሴቶች ከአካባቢው እንዲነሱ በፖሊስ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው ይላል።
ፌደራል ፖሊስ ሴቶቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ከተኮሰ በኋላ ወንዶች መጥተው ደንጋይ ወደ ፖሊስ አባላቱ መወርወር ጀመሩ ሲል ሳዳም ያየውን ለቢቢሲ ገልጿል።
ይህ የዓይን እማኝ ግርግሩን ተከትሎ ተረጋግጠው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን መመልከቱን ጨምሮ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በአሁኑ ሰዓት ምዕመኑ "ተረጋግቶ ወደ መጣበት እየተመለሰ" ነው ያለ ሲሆን የረብሻውን መነሻና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮችን ለሕዝብ አሳውቃለሁ ብሏል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ እና ፌደራል ፖሊስ ቢደውልም የሚመለከታቸውን ኃላፊ ለማግኘት አልቻለም።
ግርግሩን ተከትሎ ከወላጆች ጋር የተነጣጠሉ በርካታ ሕጻናት በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ በአካባቢው ባሉ መስጅዶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች ሆነው ወላጆቻቸውን እየተጠባበቁ እንደሆነ የማሕበራዊ ሚዲያ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጎንደር ከተማ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ሕዝበ ሙስሊሙን አስቆጥቶ ነበር።
በጎንደሩ ግጭት ከ20 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታውቆ ነበር።
ከከጎንደሩ ክስተት በኋላ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የእምነት ተቋማት ላይ ውድመት ደርሶ ነበር።
የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ.ም. በደባርቅ ከተማ ሁለት መስጅዶች እንደተቃጠሉ የገለጸ ሲሆን የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ደግሞ በስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ በተመሳሳይ ቀን ሚያዝያ 20 ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች ላይ ውድመት እንደደረሰ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።












