ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰመጠችው የሩሲያ ግዙፍ የጦር መርከብ የመጨረሻ ሰዓት
ሞስኮቫ ትባላለች፡፡
የሩሲያ ብሔራዊ ኩራት ነበረች፡፡
ከታላቋ ሶቭየት ኅብረት ጀምሮ በሕይወት ቆይታለች፡፡
በርካታ ጦርነቶችን ተሳትፋለች፡፡ በቅርቡ ጥቁር ባሕር ላይ ከዚህ ዓለም "በሞት" ተለይታለች፡፡
የአሟሟቷ ሁኔታ ዛሬም እያወዛገበ ነው፡፡ ሞስኮቫን ማን "ገደላት?"
ዩክሬኖች ራሳችን ባመረትነው ናፕቹን በሚባል ቀላል ሚሳኤል ተኩሰን ገደልናት ይላሉ፡፡
ሩሲያዊያን በበኩላቸው ወጀብ እሳት ፈጠረ፣ እሳቱ መርከቧ ከጫነችው መሳሪያ ጋር ተነካካ፣ ፍንዳታ ተከሰተ፤ ሞስኮቫ ሰጠመች፤ ይላሉ፡፡
ብዙም ሳይዘገይ የሞስኮቫን የመጨረሻ ሰዓት የሚያሳይ አነጋጋሪ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወጥቷል፡፡
ምሥሉ ሞስኮቫን ማን ለሞት እንዳበቃት በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ባያደርግም አንዳች ፍንዳታ በድንገት ሲከሰት ግን ያሳያል፡፡
ሞስኮቫ ከ40 ዓመታት በላይ አገሯን ሩሲያን ያኮራች እጅግ ሥመ ጥር፣ እጅግ ግዙፍ የጦር መርከብ ስትሆን በውስጧ 510 የባሕር ኃይል አባላትን ይዛ ነበር፡፡
ጸረ ሚሳኤል፣ የአየር መቃወሚያ፣ ጸረ ሰርጓጅ መርከብ እና ሌሎች እጅግ ውስብስብና ግዙፍ መሣሪያዎችን የጫነች አንድ ትልቅ የገበያ ሞል የምታክል መርከብ ነበረች፡፡
ከ500 በላይ የሚሆኑት የባሕር ኃይል ባልደረቦቿ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መውጣት ችለዋል፡፡
ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ምን ያሳያል?
ይህ አነጋጋሪ የኾነው ተንቀሳቃሽ ምሥል በኤፕሪል 14 እንደተቀረጸ ይታመናል፡፡
የተንቀሳቃሽ ምሥሉ ቆይታ 3 ሰኮንድ ብቻ ነው፡፡ ምናልባትም ምሥሉ የተቀረጸው ባሕርተኞቹን ለማዳን ከቆመ ሌላ የነፍስ አድን አነስተኛ ጀልባ ይሆናል፡፡
ይህ አነስተኛ ጀልባ ከሞስኮቫ በቀኝ በኩል እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡
በቪዲዮው ወዲያውኑ ጭስ ከመርከቡ ሲወጣ ይታያል፡፡
የግዙፏ መርከብ ጫፍ ከውሃ አካሉ ጋር ከሚገናኝበት ሰገነት አካባቢ ውሃ ሲዘልቅ ይታያል፡፡
ዩክሬን አሁንም ሞስኮቫን በናፕቹን ሚሳኤል ወደ ሞት እንደሸኘች ትናገራለች፡፡
ስማቸው ያልተገለጸ አንድ የአሜሪካ የጦር አማካሪ ዩክሬን ሞስኮቫ ላይ ጥቃት ስለመሰንዘሯ እርግጠኛ ሆነው ለአሜሪካ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ግን አሁንም ለሞስኮቫ መስጠም ምክንያት የሆነው በወቅቱ የነበረ አደገኛ የባሕር ወጀብ፣ ያን ተከትሎ እሳት መፈጠሩና መሳሪያ መፈንዳቱ ነው ትላለች፡፡
ቢቢሲ ይህን የ3 ሰከንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል ለሦስት ዕውቅ የባሕር ኃይል አዋቂዎች በማሳየት ምን እንደተረዱ ጠይቋል፡፡
ሦስቱም በሞስኮቫ መርከብ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡
የሚፈስ ነዳጅ የፈጠረው እሳት ይሆን?
ሪል አድሚራል ክሪስ ፓሪ የእንግሊዝን ባሕር ኃይል የመሩ ሰው ናቸው፡፡ እሳቸውም ሞስኮቫ በሚሳኤል ስለመመታቷ ጥርጣሬ አልገባኝም ብለዋል፡፡
‹‹በተንቀሳቃሽ ፊልሙ የሚታየው የመርከቧ ጫፍ ሽራፊ በሚሳኤል ስለመመታቱ ነው፡፡
እዚያው የተፈጠረ ፍንዳታ ቢሆን ኖሮ ያ ሽራፊ ወደ ውጭ ተቦድሶ ይወጣ ነበር እንጂ ወደ ውስጥ አይጣመም ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡
የቀድሞ የኔቶ ኮማንደር በበኩላቸው ከመርከቧ ሲወጣ የሚታየው ጭስ እንዴት ሊኖር ቻለ በሚል ከቢቢሲ ተጠይቀው ከሚሳኤል ጥቃት በኋላ የፈሰሰ ነዳጅ የፈጠረው ይሆናል ብለዋል፡፡
ከሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የሆኑ አንድ ሲዳርዝ የሚባሉ የጦር አዋቂ ደግሞ ተንቀሳቃሽ ምሥሉን ተመልክተው ለቢቢሲ በሰጠት አስተያየት ‹ፍንዳታው እንዲከሰት የቻለው በሚሳኤሉ ነው፡፡
ላይ ሚሳኤሉ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው የአውሮፕላን መቃወሚያ የሆኑ የጦር መሣሪያዎች ባሉበት ክፍል ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ከባድ ፍንዳታ ሊደርስ የቻለው› ብለዋል፡፡
የባሕር ወጀብ ሊሆን ይችላል?
ሩሲያ ለሞስኮቫ መስጠም ነውጥ የቀላቀለ ሞገድ አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሳ ነበር፡፡ በዚህ ተንቀሳቃሽ ምሥል ይህን የሚያመላክት አንዳችም ነገር አልተገኘም፡፡
የሞስኮቫ መስጠም ዜና ከመሆኑ በፊት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አንድ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡
መግለጫው ሞስኮቫ ላይ ጉዳት መድረሱና ባሕርተኞቿ ግን በሙሉ በሰላም መውጣታቸውን ነበር የሚያትተው፡፡
ስለ ወጀቡ ማውሳት የጀመረው ኋላ ላይ ነበር፡፡
ሩሲያ ዛሬም ድረስ ብሔራዊ ኩራት የነበረችው መርከቧ በሚሳኤል ስለመመታቷ ግን አላመነችም፡፡
ቅዳሜ ዕለት የሩሲያ መከላከያ፣ የሞስኮቫ የባሕር ኃይል አባላት በክሪሚያ ጠረፍ፣ ሰቫስታፖል ወደብ አካባቢ ወታደራዊ ትዕይንት ሲያደርጉ የሚያሳይ ምሥል አጋርቷል፡፡
እነዚህ 510 የባሕር ኃይል አባላት ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከመርከቧ ወደ ዩክሬን ከተሞች ሲወነጨፉ የነበሩ ሚሳኤሎችን ሲያቀነባብሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ማሪዮፖልን ከተማን ወደ ትቢያነት የቀየሩ ናቸው፡፡
እርግጥ ነው ሞስኮቫ ጥቁር ባሕር ላይ የሚያህላት ኃይል አልነበረም፡፡
የሩሲያ መመኪያ ሆና ዘልቃለች፡፡ እንዲህ ዓይነት ግዝፈት፣ አቅምና ጉልበት ያላቸው መርከቦች በዓለም ላይ ብዙ አይደሉም፡፡
ሞስኮቫ ከመስጠሟ ቀደም ብሎ ታዲያ ስኔክ ወደብ የሚገኙ የዩክሬን ጥቂት ወታደሮችን እጅ እንዲሰጡ ታስጠነቅቃለች፡፡ እምቢኝ አሻፈረኝ ካሉ ግን ልትፈጃቸው እንደሆነ መልእክት ትሰዳለች፡፡
በስኔክ ደሴት የነበሩት አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው የዩክሬን ወታደሮች ታዲያ በምላሹ አንድ አስደንጋጭ መልእክት ለሞስኮቫ ላኩ፡፡
‹‹ገሃነም ግቢ›› የሚል፡፡
እርግማናቸው ደርሶ ይሆን? ሞስኮቫ የሰጠመችው?