ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ ግዙፏ የጦር መርከብ በጥቁር ባሕር ሰመጠች
ለሩሲያ ትልቅ ብሔራዊ አርማና ብሔራዊ ኩራት ሆና የቆየችውና ሞስኮቫ በሚል ስም የምትታወቀው እጅግ ግዙፏ የጦር መርከብ በጥቁር ባሕር ሰመጠች፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ባወጣቸው መገለጫ ሞስኮቫ የሰጠመችው ረቡዕ ዕለት በፍንዳታ ከተጎዳች ከሰዐታት በኋላ ነው፡፡
ከፍንዳታው በኋላ ጥገና እንዲደረግላት ወደ ሰቨስተፖል ወደብ አካባቢ እየተጠጋች ነበር ተብሏል፡፡ ኾኖም የባሕር ወጀብ አንገላቷት መቋቋም ባለመቻሏ መስመጧን ሩሲያ አምናለች፡፡
በሞስኮቫ የነበሩ ከ500 በላይ የሩሲያ ባሕር ኃይል አባላትም ወደ ሌላ መርከብ ተወስደው ሕይወታቸው መትረፉም ተነግሯል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ የዝነኛዋና ታሪካዊቷን መርከብ ሕይወት የቆረጥኩት እኔ ነኝ እያለች ነው፡፡
ሞስኮ ግን ይህን ታስተባብላለች፡፡
ሞስኮቫ ዕድሜዋ 40 ዓመት ያለፈው ሲሆን በጥቁር ባሕር የጦር መርከብ የሩሲያ መተማመኛና ብሔራዊ ኩራት ተደርጋ የምትታይ ነበረች፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ አዛዦች ሞስኮቫን ኔፕቱን የሚባል ሚሳኤል በማስወንጨፍ ነው መርከቧ ላይ ጉዳት ያደረስነው ይላሉ፡፡
ኔፕቱን ሚሳኤል ሩሲያ ክሪሚያን በ2014 እ.አ.አ ከያዘች በኋላ በጥቁር ባሕር አካባቢ ያለባትን የደኅንነት ስጋት ለመቅረፍ ዩክሬን ያመረተችው ተወንጫፊ መሣሪያ ነው፡፡
አንዳንድ የጦር አዋቂዎች ኔፕቱን ሚሳኤል ሩሲያ በአካባቢው ያላትን ውስብስብ የአየር መቃወሚያ አልፎ ግዙፏን የጦር መርከብ ሞስኮቫን ሊመታ ስለመቻሉ ይጠራጠራሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ ሞስኮቫን ለዚህ የዳረጋት ምን እንደሆነ ከገለልተኛ ወገን እስከ አሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
ሞስኮቫ የጦር መርከብ በሶቭየት ኅብረት ጊዜ ተገንብታ ወደ ሥራ የተሠማራቸው እንደ አውሮጳዊኑ በ1980ዎቹ ነበር፡፡
ሞስኮቫ ግዙፍ ሚሳኤል ተሸካሚ የጦር መርከብ በሶሪያ ግጭት ጊዜ የሩሲያ ወታደሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ማገዟ ይነገራል፡፡
እጅግ ውስብስብና ግዙፍ የጦር መሣሪያዎችን መሸከም የምትችለው ሞስኮቫ ከ12ሺህ ቶን በላይ ክብደት አላት፡፡
እንዲህ ዓይነት ግዙፍ የጦር መርከብ ሲሰጥም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሞስኮቫ የመጀመርያዋ ናት፡፡