ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የዩክሬኑ ጦርነት አፍሪካ በምግብ ራሷን እንድትችል ዕድል ይፈጥራል" አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት አፍሪካ በምግብ አቅርቦት ራሷን እንድትችል "ትልቅ ዕድል" እንደሚፈጥር ተናገሩ።
አሊያንስ ፎር ኤ ግሪን ሪቮሉሽን አፍሪካ (ኤጂአርኤ) የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ኃይለማርያም፤ የዩክሬኑ ጦርነት ከምግብ፣ ከነዳጅ እና ማዳበሪያ ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ በመላው አፍሪካ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከዩክሬኑ ጦርነት በፊት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት እንዲሁም በአህጉሪቱ በአንዳንድ አገራት ግጭት ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ የምግብ አቅርቦትና ክምችት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነበር ብለዋል።
"ወደ 36 በሚሆኑ አገራት፣ 90 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ረሃብ ገጥሞታል" ብለዋል።
ከመነሻውም የምግብ ደኅንነታቸው አስተማማኝ ባልሆኑ አገራት የዩክሬኑ ጦርነት ያሳደረው ተጽዕኖ ሲጨመር ደግሞ ችግሩ የበለጠ እንደተባባሰ አክለዋል።
"በተለይም ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ወደ አገራቸው ከውጭ እስከሚገቡ የሚጠባበቁ የአፍሪካ አገራት ብዙ ናቸው" ብለዋል አቶ ኃይለማርያም።
አቶ ኃይለማርያም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በጊዜ ሂደት አፍሪካ በምግብ ምርት ራሷን መቻል እንዳለባት ገልጸዋል።
"አፍሪካ ውስጥ ከዓለም 60% የሚሆነው የሚታረስ መሬት ይገኛል። ነገር ግን ጥቅም ላይ አልዋለም። አሁን ላይ የአፍሪካ መሪዎች ቆርጠው ተነስተዋል። አፍሪካውያን ነጋዴዎችም ሁኔታውን ተገንዝበዋል።"
የአህጉሪቱ መሪዎች አገር በቀል ግብርናን ለማዘመን እምብዛም ትኩረት ሲሰጡ እንደማይስተዋል እና ወረቀት ላይ ጥሩ የግብርና ፖሊሲዎች ቢኖሩም መሬት ላይ ወርደው ሲተገበሩ እንደማይታይ በመጥቀስ፣ አፍሪካ 1.2 ቢሊዮን ዜጎቿን መመገብ ትችላለች ወይ? ሲል ቢቢሲ ለአቶ ኃይለማርያም ጥያቄ አንስቷል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በምላሻቸው "መልሱ ግልጽ ነው። መልሱም አዎ፣ መመገብ ትችላለች ነው" ብለዋል።
በእሳቸው አስተያየት፣ አፍሪካ ውስጥ ግብርናን ለወጣቶች ማራኪ አድርጎ ማቅረብ ያስፈልጋል።
"በአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ ቅርጽ እየያዘ ይገኛል። ወጣቶቻችን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ቅርብ ናቸው። መመንደግ የምንችለውም ከዚህ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።
የአየር ሁኔታን፣ አካባቢን እንዲሁም ሌሎችም መረጃዎችን ሰብስቦና አብላልቶ፣ ብልህ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚተገበረውን የግብርና አሠራር አቶ ኃይለማርያም ጠቅሰዋል።
"ዲጂታል መንገድ በመጠቀም በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚያግዝ አሠራር ነው። በቀላሉ ለውጥ እንዲመዘገብ የሚረዳውም ይህ ነው ብዬ አስባለሁ።"
በዚህ ሂደት ውስጥ ለአፍሪካ ግብርና መሠረት የሆኑት በአነስተኛ ደረጃ ያሉ አርሶ አደሮች መዘንጋት እንደሌለባቸውም አያይዘው ገልጸዋል።