ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመጀመሪያዎቹ የዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሳምንታት ውስጥ ሩዋንዳ ሊገቡ ይችላሉ
የመጀመሪያዎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሳምንታት ውስጥ ከእንግሊዝ ወደ ሩዋንዳ ሊወሰዱ እንደሚችሉ መንግሥት አስታውቋል።
የእንግሊዝ መንግሥት ጥገኝነት የሚጠይቁ ግለሰቦች ጉዳያቸውን ለማሳለጥ ወደ ምስራቃዊቷ አገር ሩዋንዳ እንደሚልክ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ በሳምንታት ውስጥ ይደርሳሉ የተባለው።
ይህ እቅድ መጀመሪያ ላይ የሚያተኩረው ከፈረንሳይ በጀልባ ወይም በጭነት መኪናዎች ተጭነው የቻናል ደሴቶችን አቋርጠው ወደ እንግሊዝ በሚገቡ ቤተሰብ በሌላቸው ወንዶች ነው።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሂደት "ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ህይወቶች ይታደጋል" እንዲሁም የህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎችን ንግድ ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል ቢሉም ተሟጋቾች በበኩላቸው እቅዱን "ኢሰብአዊ" ሲሉ ጠርተውታል።
የቢቢሲው ሲሞን ጆንስ እንደገለጸው አርብ ማለዳ ላይ ሁለት ተጨማሪ የስደተኞች መሻገሪያዎች ተመዝግቧል።
የፓርላማ አባሉና ቁጥር 10 የተባለው ፖሊሲ ዳይሬክተር አንድሩው ግሪፍዝ እንደገለጹት እቅዱ አዲስ ህግ ማርቀቅ የማያስፈልገውና በ "ነባር ስምምነቶች" ሊተገበር የሚችል ነው ብለዋል።
የፓርላማ አባሉ እንግሊዝ ጥገኛ ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሂደትን አስመልክቶ ለቢቢሲ ኒውስናይት እንደተናገሩት በሳምንታት ውስጥ ወይም በጥቂት ወራት ውስጥ ሊጀመር ይችላል ብለዋል።
አክለውም የህገ-ወጥ ስደት ፍሰቱን ማቆም ከተቻለ ወደ እንግሊዝ ለመግባት ደህንነቱ የተጠበቀ እና ህጋዊ መንገዶች ብቻ ምርጫ ይሆናል ብለዋል።
ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ የመጣው በትናንሽ ጀልባዎች የቻናል ደሴቶችን በማቋረጥ ወደ እንግሊዝ የሚገቡትን ሰዎች ቁጥር የመቀነስ ሰፊ ስትራቴጂ አካልም ነው ተብሏል።
የሮያል ባህር ኃይል ወደ እንግሊዝ የሚያመራውን እያንዳንዱን ጀልባ ለማወቅም በቻናል ያለውን ስራ በሙሉ ከዩናይትድ ኪንግደም የድንበር ኃይል በመውሰድ በዋነኝነትም እየተቆጣጠረ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት 28 ሺህ 526 ሰዎች ቻናልን ተሻግረው ወደ እንግሊዝ የገቡ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2020 ቁጥሩ 8 ሺህ 404 ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም የድንበር ሃይል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ቶኒ ስሚዝ ስር ነቀል ብለው የጠሩት ይህ እቅድ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑ ግልፅ ከመሆኑ በፊት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል ብለዋል ።
የቀድሞው ዳይሬክተር ለቢቢሲ ብሬክፋስት እንደተናገሩት ግለሰቦች ወደ ሩዋንዳ የሚሄዱ አውሮፕላኖች ላይ ሲጫኑ የአንግሊዝ መንግሥት ህጋዊ ፈተና ሊገጥመው ይችላል።
"ነገር ግን ጀልባዎቹን ለማስማቆም ምን ማድረግ እንዳለብን እርግጠኛ አይደለሁም… ምክንያቱም አንድ ነገር ካላደረግን ብዙ ሰዎች ሰጥመው ይሞታሉ" በማለት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሃሙስ ዕለት ባደረጉት ንግግር ከሩዋንዳ ጋር የተደረገው ስምምነት "ለጥገኝነት ጠያቂዎች አስተማማኝ እና ህጋዊ መንገዶችን ይሰጣል" ብለዋል።