ቡሩንዲ በቢቢሲ ላይ ጥላ የነበረውን የሶስት ዓመት እገዳ አነሳች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቢቢሲ ከሶስት ዓመታት እገዳ በኋላ በቡሩንዲ ስራውን ጀምሯል።
የቡሩንዲ የሚዲያ ባለስልጣን፣ ብሄራዊ የኮሙኒኬሽን ምክር ቤት (ሲኤንሲ) በያዝነው ሳምንት ረቡዕ በንግድ ከተማዋ ቡጁምቡራ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላም እገዳው መነሳቱን አስታውቋል።
ቢቢሲ ከሶስት ዓመት በፊት በአገሪቱ የተሰጠው ፈቃድ የተነጠቀ ሲሆን ዘጋቢዎችም በአገሪቱ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ወይም ለዜና አገልግሎቱ መረጃ ማቀበል አይቻልም ነበር።
ቡሩንዲ ከቢቢሲ ጋር እሰጣገባ የገባው አገሪቷ የተቃዋሚዎችን ድምጽ ለማፈን ሚስጥራዊ የማሰቃያ ጣቢያዎችን ትጠቀማለች በሚል የምርመራ ዘገባ መስራቱን ተከትሎ ነው።
ቡሩንዲ ሃሰተኛ ዘገባ ነው በማለት ከማጣጣል በተጨማሪ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሪንዚዛን መንግሥት ስም አጠልሽቷል በማለት ወቅሳለች።
በእገዳው ወቅት ቢቢሲ በሃገሪቱ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ተመልካቾች እና አድማጮች ነበሩት።
ይህ እርምጃ በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ የተወገዘ ሲሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ ባወጣው መግለጫ "የቡሩንዲ ባለስልጣናት የመገናኛ ብዙኃንን ዝም ለማሰኘት የጀመሯቸው ጥረቶች አካል ነው" በሚልም ወቅሷል።
የሲኤንሲ ኃላፊ ቬስቲን ናሂማና ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ቢቢሲ የሬዲዮ ስርጭቱ እንዲጀመር ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ስራ እንዲጀምር ውሳኔ ላይ መደረሱን ነው።
ኃላፊዋ አክለውም የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ማዕቀብ በተጣለባቸው የዜና ማሰራጫዎች ላይ ገደቦችን ቀለል ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
አገሪቷን እየመሩ ያሉት ኢቫሪስቴ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የመረጧቸው ተተኪ ናቸው። ከሁለት አመታት በፊት በምርጫ ካሸነፉ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ባልተጠበቀ ሁኔታ በስልጣን ላይ እያሉ የሞቱትን ፕሬዚዳንት ንኩሪንዚዛንም የተኩት ከተጠበቀው ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው።
የእሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ህብረት ጋር የነበረው ግንኙነት መለሳለስ አሳይቷል።
እንዲሁም በአገሪቷ ይታይ የነበረው ብጥብጥ መቀነሱና እንዲሁም በነበሩ ማሻሻያዎች ምክንያት አሜሪካ ጥላ የነበረችውን ማዕቀብም አንስታለች።












