ፀጉር እንዲነቃቀል የሚያደርገው አሎፒሺያ ምንድን ነው? ሕክምናስ አለው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"ስለ አሎፒሺያ የፈለጋችሁትን በሉ። ነገር ግን ደርሶባችሁ እስክታዩት አታውቁትም። መንፈስ ሰባሪ በሽታ ነው" ትላለች ኤሚ ቺኒክ።
ኤሚ ከ21 ዓመተ ጀምሮ ነው ይህ በሽታ ፀጉሯን ይጨርሰው የጀመረው።
ክሪስ ሮክ የተባለው አንጋፋ ኮመዲያን ይህን በሽታ ተንተርሶ የሰነዘረው ቀልድ የሷን ሕይወት ያስታውሳታል።
ከበርካታ ዓመታት ልፋት በኋላ በፊልም ዘርፍ ትልቁ የተባለውን የኦስካር ሽልማት ያገኘው ዊል ስሚዝ የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል።
የዊል ስሚዝ ሚስት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ የዚህ በሽታ ተጠቂ ናት።
ዊል ስሚዝ ኮመዲያኑ ክሪስ ሮክ የሚስቱን መመለጥ ተመልክቶ የሰነዘረው ጉሸማ አልዋጥ ብሎት በጉምቱ ተዋንያን ፊት የሙያ አጋሩን በጥፊ አጩሎታል።
ዊል፤ ክሪስ ሮክን በጥፊ አንገቱ እስኪዞር ሲያጋጨው የሚያሳየው ምስል በመቶ ሚሊዮኖች ታይቷል።
የዓለም ሕዝብ በጥፊው ምክንያት ለሁለት ተከፍሏል።
ግማሹ እሰየው ክሪስ ሮክ ሲያንሰው ነው ይላል። የተቀረው ደግሞ ጡጫን ምን አመጣው ሲል ይሞግታል።
አሎፒሺያ የተባለው በሽታ ያለባቸው ሰዎች ግን ስለበሽታው ግንዛቤ እንዲኖር ጥፊው ጠቅሞናል የሚሉ ይመስላሉ።
የ26 ዓመቷ ኤሚ ክሪስ ሮክ የጄዳን ስም አንስቶ ማብጠልጠሉ ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም ትላለች።
"ትንሽ መስመር አልፎ ወጥ ረገጠ" ትላለች ኤሚ የክሪስ ሮክን ድርጊት በመኮነን።
ኤሚ ቅጥያ ፀጉር ሳታደርግ ከቤቷ አትወጣም።
"በፍፁም አያስቅም። ሌላ በሽታ ተንተርሶ እንደማይቀልደው ሁሉ በዚህም ላይ መቀለድ አልነበረትም። ጉዳዩ ቀልድ አይደለም" ትላለች።
"እርግጥ ነው አሎፒሺያ ለሞት ላይዳርግ ይችላል። የሚያስከትለው የአእምሮ መቃወስ ግን ቀላል አይደለም።"
ኤሚ መላ ፀጉሯን ያጣችው በሦስት ሳምንታት ውስጥ ነው። መጀመሪያ አንድ ሁሉት ዘለላ ተንቅሎ መውደቅ ጀመረ። ቀጥሎ ግን ሁሉም ረገፈ።
ልክ እንደ ጄዳ ፒንኬት ሙሉ ፀጉሯ ተነቅሎ አልቋል። ነገር ግን ከስድስት ዓመታት በኋላ እንኳ ያለምንም ልባስ መውጣት አትችልም።
ኤሚ የዊል ስሚዝ በክሪስ ሮክ ንግግር መቆጣቱ ይገባኛል ትላለች።
"እሱም ልክ እንደኔ የፍቅር አጋር ብዙ ዓይቶ ይሆናል" ስትል አመክንዮዋን ታስቀምጣለች።
"ዘውትር ጠዋት ከአልጋ ስወርድ እንባ ይቀድመኛል። ምን ያህል ፀጉር እንዳጣሁ ለፍቅረኛዬ አሳየዋለሁ። ወደ ውጪ ላለመውጣት ምክንያት እፈልጋለሁ። ዊል ስሚዝም የጄዳ ስቃይ ገብቶት ይሆናል።"
ኤሚ የዊል ስሚዝ ጥፊ ሰዎች ስለበሽታው ያላቸው ግንዛቤ ጨምሮ እንደሆን ተስፋ ታደርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, AMY CHINNICK
አሎፒሺያ ምንድነው?
አሎፒሺያ የፀጉር መነቃቀል የሚያስከትል በሽታ ነው።
በሽታው በጭንቀት አሊያም በሌላ በሽታ ምክንያት እንዲሁም ከንጥረ ነገር እጥረት ሊመጣ ይችላል።
በሽታው ፆታም ሆነ ዕድሜ አይለይም። ማንኛውም ሰው በየትኛውም ዕድሜ በዚህ በሽታ ሊጠቃ ይችላል።
ቢሆንም ዕድሜያቸው ከ30 አስከ 60 ባሉ ሰዎች ላይ ይበረታል።
ነገር ግን ከሦስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በበሽታው ብዙም አይጠቁም።
ይህ በሽታ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቢያንስ 65 ሺህ ሰዎችን እንዳጠቃ ይታመናል።
የተለያዩ ዓይነት የአሎፒሺያ በሽታዎች አሉ። አንዳንዱ ዓይነት አሎፒሺያ ጥቂት ፀጉር ብቻ ሊያሳጣ ይችላል። ፀጉር መልሶ ሊበቅልም ይችላል።
ምንም እንኳ በሽታው ብዙ ጊዜ ጭንቅላት ያለ ፀጉርን ያጥቃ እንጂ ማንኛውም ፀጉር አብቃይ የሰውነታችን ክፍል ሊጠቃ ይችላል።
ብዙውን ጊዜው በሽታው እንዳለብን የምናውቀው በርከት ያለ ፀጉር ከጭንቅላታችን ተነቃቅሎ ሲወድቅ ነው።
ሕክምና
ዌብኤምዲ የተሰኘው ታዋቂ የጤና እክሎች ምክንያትና መከላከያ የተመለከቱ መረጃዎች የሚያቀብለው ድረ-ገፅ በሽታው መድኃኒት አለው ይላል።
ነገር ግን የመጀመሪያው እርምጃ የበሽታው ምልክት ሲታይ ሐኪምዎን ማማከር ነው።
ሐኪምዎ በሚያዝዎ መሠረት መድኃኒቶች መጠቀም አንደኛው አማራጭ ነው።
ሌላኛው በሽታውን ማከሚያ መንገድ ጭንቅላታችን ፀሐይ እንዳይበረታበት ሰው ሰራሽ ፀጉርን ጨምሮ ሌሎች መሸፈኛዎችን መጠቀም ነው።
ጭንቀት መቀነስ ይህ በሽታ ለሚያጠቃቸው ሰዎች ይመከራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images















