ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሴት የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ የተከናወኑ 23 ቀዶ ሕክምናዎች
የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በሴት የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ 23 የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች አከናውኗል።
በዚህም ኮሌጁ ሴት ሐኪሞች ብቻ በተካተቱባቸው ሰባት የቀዶ ሕክምና ቡድኖች ለ23 ያህል ሕሙማን ቀዶ ሕክምና አድርጓል።
በሕክምና ቡድኖቹ ከቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶች እስከ ጽዳት ሠራተኞች ድረስ ሴቶች ብቻ ተሳታፊ እንደነበሩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኃላፊዎች ገልጸዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የሜዲካል አገልግሎት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ በዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በሆስፒታሉ በሴት ባለሙያዎች ብቻ የቀዶ ሕክምናዎች የተከናወኑት አንድም የሆስፒታሉን ሰባ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር በሚል መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዕለቱ በሴት ባሙያዎች በተካተቱባቸው ቡድኖች 21 ቀዶ ጥገናዎችን ማከናወናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ሊዲያ፣ በአጠቃላይ የቀዶ ሕክምናውን ለሕጻናት፣ ለእናቶች እና ለአዛውንቶች መሰጠቱን ገልፀዋል።
ዶ/ር ሊድያ አክለውም ከዚህ ቀደም በተከናወኑ በርከታ የቀዶ ሕክምናዎች ሐኪሞች፣ ነርሶች እና ሌሎች አጋዥ ሴት ባለሙያዎች የነበሩ ቢሆንም፤ በዚያ ዕለት ግን በሴቶች ብቻ መካሄዱ አንዲሁም ከሌላው ጊዜ በርከት ያለ ቀዶ ሕክምና መካሄዱ ለየት ያደርገዋል ይላሉ።
በዕለቱ የቀዶ ሕክምና ክፍል አስተባባሪ የነበሩት በጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ጥገና ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መሠረት ሺበሺ ናቸው።
እርሳቸው ባስተባበሩት ክፍል ውስጥ ሰባት የቀዶ ሕክም ክፍሎች እንደነበሩ ያስታወሱት ዶ/ር መሠረት፣ በእነዚህ ክፍሎችም 23 አይነት ቀዶ ሕክምናዎችን ሲያከናውኑ መዋላቸውን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ገልፀዋል።
በእነዚህ ላይም የቀዶ ሕክምና፣ የሰመመን ባለሙያዎች፣ ነርሶች፣ ጽዳት ሠራተኞች፣ የማንቂያ ክፍል ባልደረቦች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል።
እነዚህ ሁሉ ሥራዎች በዕለቱ የተሸፈኑት በሴቶች እንደነበርም አክለው ገልፀዋል።
ዶ/ር ሊድያ በበኩላቸው በእያንዳንዱ የቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ ቢያንስ ሁለት የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች፣ ሦስት ነርሶች እንዲሁም የጽዳት ሠራተኞች እንደነበሩ አክለዋል።
ዶ/ር ሊድያ በእያንዳንዱ የቀዶ ሕክምና ክፍል ቢያንስ ሦስት ቀዶ ሕክምናዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ዶ/ር መሠረትም የሐሞት ከረጢት ጠጠር፣ የእንቅርት እና ቫሪኮስ ቬን ለማስወገድ በተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ላይ ተሳትፈዋል።
ዶ/ር ሊድያ እንደተናገሩት ከሆነ በዕለቱ የሁለት ወር ዕድሜ ካለው ጨቅላ ህጻን ጀምሮ፣ ከፍተኛ የሆነ የማህፀን ዕጢ ሕክምና፣ የሐሞት ጠጠር፣ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና እና ሌሎች የቀዶ ሕክምናዎች መሰጠታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ በሴቶች ብቻ የተካሄዱት የቀዶ ሕክምናዎች እንደ ዓላማ "ዕለቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከመሆኑ አንጻር ሴቶች ከተማሩ፣ ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ እና የሚፈልጉበት ዓላማ ላይ ለመስራት ከቆረጡ የሚያቅታቸው ነገር የለም የሚለው መልዕክት ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ለማለፍ ነው" ይላሉ ዶ/ር ሊድያ።
ሕክምና ሴቶች አይደፍሩትም ተብለው ከሚታሰቡ ሙያዎች መካከል አንዱ ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ "በተለይ ከሕክምናም የቀዶ ሕክምናን ሴቶች አይደፍሩትም ብለው የሚያስቡ አንዳነድ ሰዎች አሉ" ይላሉ።
ዶ/ር መሠረት ቀዶ ሕክምና ማድረግ በየዕለቱ የሚሰሩት ተግባር መሆኑን አስታውሰው፣ በዓለም አቀፍ ሴቶች ዕለት ያከናወኑት ይህ የቀዶ ሕክምና የሚለየው ሴቶች ብቻ የተሳተፉበት በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል።
በዕለቱ ያከናወኗቸው ሕክምናዎች በአጠቃላይ የተሳኩ እንደነበር አስታውሰው፣ ለሌሎች ሴቶች ምሳሌና አርዓያ በመሆን ረገድም ቢሆን ውጤታማ ሥራ ማከናወናቸውን ይናገራሉ።
ተለቅ ያሉ የቀዶ ሕክምናዎች በወንዶች የሚሰሩ ለሚመስለው የኅብረተሰብ ክፍል በሴቶችም እንደሚከናወን እና ሴቶች በሁሉም መስክ የተዋጣላቸው ባለሙያዎች እንደሆኑ በማሳየት ረገድ ውጤታማ እንደነበሩ አበክረው ተናግረዋል።
ዶ/ር ሊድያ በበኩላቸው ታዳጊ ሴቶች በትምህርታቸው እንዲተጉ፣ በሥራ ላይ ላሉም መልካም አርዓያ ለመሆን እንዲሁም በየቤቱ ወልደው ልጆቻቸውን እያሳደጉ ላሉ እናቶች በልጆቻቸው ምክንያት ከዓላማቸው ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ለማስታወስ ይህንን ማድረጋቸውንም ይናገራሉ።
በዕለቱ የነበረው አጠቃላይ ድባብ ደስ የሚል እንደነበር የሚያስታውሱት ዶ/ር ሊድያ፣ የቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው ግለሰቦችም በአጠቃላይ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ዶ/ር ሊድያ በሕክምናው ዘርፍ በአጠቃላይ 11 ዓመት ያህል መቆየታቸው ገልፀው፤ በጤናው ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
በአነስተኛ የሕክምና ተቋማትም ሆነ በትላልቅ ሪፈራል ሆስፒታሎች ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ ሚና ቢኖራቸውም፣ አጠቃላይ በሕክምና ሙያ ዘርፍ ከወንዶች አንጻር ሲታይ የሴቶች ቁጥር ዝቅ ያለ ነው የሚሉት ዶ/ር መሠረት፣ በየደረጃው ቁጥራቸውን ከፍ ለማድረግ የኅብተረተሰብ እና የመንግሥት ድጋፍ አስፈላጊነትን ይጠቅሳሉ።
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ዶ/ር ሊድያ ሴቶችን ማስተማር እና መደገፍ ብቻ ሳይሆን በትምህርታቸው እየገፉ እንዲሄዱ፣ በተቋማት ባሉ የእድገት መሰላሎች ወደላይ እንዲወጡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውሰዋል።
ዶ/ር ሊድያ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሆስፒታል በአመራር ላይ የሚገኙ ሴቶችን ቁጥር ለመጨመር እንዲሁም ነርሶች በተሰማሩበት ዘርፍ ስፔሻላይዝ እያደረጉ እንዲሄዱ ለማድረግ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ።