ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ የገቡ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ8 በላይ ሰዎች ተገደሉ

ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የገቡ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከስምንት ሰዎች በላይ ሲገደሉ አምስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገለጸ።
የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ አቶ ኦጌቱ አዲንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከደቡብ ሱዳን የተነሱት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሲሆኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻግረው በመግባት ነው።
ኃላፊው ጨምረውም የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ.ም ድንበር አቋርጠው በመግባት በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ በካንካን ቀበሌ ውስጥ በመጀመሪያ መንገድ ላይ ሲጓዝ በነበረ አምቡላንስ ላይ በደፈጣ ተኩስ ከፍተው ሦስት ሰዎችን ገድለዋል።
በማስከተልም የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎቹ ወደ መንደር በመግባት ድንገተኛ ተኩስ መክፈታቸው የተነገረ ሲሆን ተጨማሪ አምስት ሠዎች ሲገድሉ ሌሎች 5 ሠዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የመቁሰል ጉዳት ማድረሳቸውን አቶ ኦጌቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በተጨማሪም ባለፈው እሁድ ጥር 08/2014 ዓ.ም በአቦቦ ወረዳ ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት አንድ የአካባቢው የፖሊስ አባልን በመግደል ከሰባ በላይ የአርብቶ አደሮችን ከብቶች መዝረፋቸውን ኃላፊው ተናገረዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻን በማሰማራት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ሥራውን እየተከናወነ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ መናገራቸው ተዘግቧል።
የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ እንዳሉት ይህ ወቅትን ተከትሎ የሚፈጸመው ጥቃት በተለይ በበጋ ወራት ውስጥ እንደሚያጋጥም ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜ በጋምቤላ ክልል በጋ በመሆኑ ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያጋራው ሰፊ ድንበር በኩል የሙርሌ ታጣቂዎች በቀላሉ በመግባት ጥቃት ይፈጽማሉ ብለዋል።
በደቡብ ሱዳን የሚገኙት የሙርሌ ጎሳ አባላት የሆኑት ታጣቂዎች ከዚህ በፊትም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በጋምቤላ ክልል ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።
ከዓመታት በፊት በኑዌር ዞን እና አኙዋ ዞኖች ውስጥ በመግባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት አፍነው ሲወስዱ፣ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ ሰዎች ደግሞ ገድለው ነበር።
ታጣቂዎቹ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚወሰነው የጋምቤላ ክልል ውስጥ በመግባት በነዋሪዎች ላይ ከሚፈጸሙት ጥቃት በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የቀንድ ከብቶች በተደጋጋሚ ዘርፈው እንደሚወስዱ ፖሊስ ገልጿል።












