በላይቤሪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተከሰተ መገፋፋት ቢያንስ 29 ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

መስቀል እና መጽሃፍ ቅዱስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ላይቤሪያ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የጴንጤቆስጣል ቤተ-ክርስቲያን በተከሰተ መገፋፋት ሳቢያ ቢያንስ 29 ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ።

ከሟቾቹ መካከል 11 ታዳጊዎች እና አንዲት ነፍሰ ጡር እናት ይገኙበታል ተብሏል።

የቤተ-ክርስቲያኗ ምዕመናን በርካታ ሕዝብ በሚኖርበት የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኘው ስፍራ ለአምልኮ እና ለፀሎት ተሰባስበው ነበር ተብሏል።

ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ለቤተ-ክርስቲያኗ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ አንድ የተደራጀ የወንበዴ ቡድን አባላት መዕመናኑን መቀላቀላቸው ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር ይላል።

ከወሮበሎቹ መካከል ስለት የያዙ ይገኙበታል ተብሏል። ፖሊስ የቡድኑ አባል ነው ያለውን አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከላይቤሪያ መዲና ሞንሮቪያ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው እራሱን ሐዋሪያው አብረሃም ብሎ በሚጠራው ግለሰብ ወደ ሚመራ ግለሰብ ተሰባሰበው ነበር።

እራሱን ሐዋሪያ ብሎ የሚጠራው ይህ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰብ የራዲዮ ጣቢያም የሚያስተዳድር ሲሆን፤ ተከታዮቹ ሰዎችን ከህመም እንደሚፈውስ እና በፀሎቱም ሰዎችን መርዳት እንደሚችል ያምናሉ።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ሞሰስ ካርተር የቤተ-ክርስቲያኗ መሪ ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ምርመራ እየተደረገበት ነው ብለዋል።

የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ጆርጅ ዊሃ አደጋው ያጋጠመበትን ስፍራ ዛሬ ይጎበኛሉ ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት ሃይማኖታዊ የፀሎት መርሃ ግብሮች የተለመዱ ናቸው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በላይቤሪያ በተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖች የሚፈጸም ጥቃት እየተበራከተ መጥቷል።

ላይቤሪያ ለረዥም ጊዜ በቆየ የእስር በእስር ጦርነት ውስጥ መቆየቷ ይታወሳል።