ካዛኪስታን፡ የተባባሰውን አለመረጋጋት ተከትሎ የካዛኪስታን መንግሥት የሩስያን ድጋፍ ጠየቀ

ፖሊሶች መሣሪያ አቀባብለው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ካዛኪስታን ውስጥ ፀረ-መንግሥት ሰልፎች በተጧጧፈበት በአሁኑ ወቅት አገሪቱን "ለማረጋጋት" በሩሲያ የሚመሩ ወታደሮች ሊሠማሩ ነው።

ፕሬዝደንት ካሲም-ጆማርት ቶካዬቭ በአገር አቀፍ ደረጃ የተባባሰውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር ሴኩሪቲ ትሪቲ ኦርጋናይዜሽን (ሲኤስቲኦ) ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በነዳጅ ዋጋ መናር የተቀጣጠለው ተቃውሞው በሂደት የፖለቲካ ጥያቄዎችን በማካተት ተባብሷል።

ፕሬዚደንት ቶካዬቭ ብጥብጡን በውጭ የሰለጠኑ "የአሸባሪ ቡድኖች" ተግባር ነው ብለውታል።

በለንደን የሚገኘው ቻታም ሐውስ የመካከለኛው እስያ ኤክስፐርት የሆኑት ኬት ማሊንሰን በበኩላቸው የተቃውሞ ሰልፎቹ "የካዛኪስታን መንግሥት አገቱን ለማዘመን እና ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ከፍተኛ ብስጭት እና ቁጣን ማሳያ ነው" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ የሌሊት ሰዓት እላፊ ገደብ እና መሰባሰቦችን ጨምሮ ሌሎች ክልከላዎችን የሚጥል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ለተቃውሞ ሰልፎቹ ጠንከር ያለ ምላሽ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።

ሐሙስ ማለዳ ላይ በቴሌቭዥን የተላለፈ ንግግራቸው ሲኤስቲኦ [ሩሲያ እና አምስት የቀድሞ የሶቪየት መንግሥታትን ያቀፈ ወታደራዊ ኅብረት ነው] አገሪቱን ለማረጋጋት እርዳታ እንዲያደርግላቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

የሲኤስቲኦ ሊቀመንበር የሆነችው አርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን ረቡዕ ዕለት በፌስቡክ በሰጡት መግለጫ ኅብረቱ የሠላም አስከባሪ ኃይሎችን "ለተወሰነ ጊዜ" እንደሚልክ አረጋግጠዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካዛክስታን ያለውን ሁኔታ "በቅርበት እየተከታተለ" መሆኑን ጠቅሶ ቃል አቀባዩ ባለሥልጣናት እና ተቃዋሚዎች ካላስፈላጊ ድርጊት እንዲታቀቡ አሳስቧል።

ፕሬዚደንት ቶካዬቭ ካዛኪስታንን እአአ በ1991 ነጻነቷን ካወጀች በኋላ አገሪቱን እየመሩ ያሉ ሁለተኛው ግለሰብ ናቸው። እአአ በ2019 ሲመረጡ ዴሞክራሲያዊ መስፈርቶች በዝቅተኛ ደረጃ የተከበሩበት ነበር ሲል በአውሮፓ የደኅንነት እና ትብብር ድርጅት (ኦኤስሲኢ) ሂደቱን አውግዟል።

አደባባይ የወጡት ዜጎች አብዛኛው ቁጣቸው ያነጣጠረው ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ በብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ ቁልፍ ሚና በያዙት የቀድሞው መሪ ኑርሱልታን ናዛርባይቭ ላይ ይመስላል። እየጨመረ የመጣውን አለመረጋጋት ለማርገብ በማሰብ ረቡዕ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።

ተቃዋሚዎች የናዛርቤዬቭን ስም ሲጠሩ የነበረ ሲሆን የቀድሞውን መሪን ግዙፍ የነሐስ ሐውልት ለማፍረስ ሲሞክሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ድር አምባ ላይ ተሰራጭቷል። እንደ ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ዘገባ ከሆነ አሁን የፈረሰው ሐውልት የናዛርባይቭ የትውልድ ክልል በሆነችው ታልዲኮርጋን የቆመ ይመስላል።

የካዛክስታን ትልቁ አየር ማረፊያ ሠራተኞች የመንግሥት ህንጻዎችን ዒላማ ካደረጉት የፀረ-መንግሥት ተቃዋሚዎችን ሲሸሹ ታይተዋል።

ተቃዋሚዎች በአልማቲ በሚገኘው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ከተሰባሰቡ በኋላ ወረራ ፈጽመውበታል። በማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች ከህንጻው ከፍተኛ ጭስ ሲወጣ ያሳዩ ሲሆን የተኩስ ድምጽም ይሰማ ነበር።

የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ካናት ታይመርዴኖቭ በበኩላቸው "ጽንፈኞች እና አክራሪዎች 500 ሠላማዊ ዜጎችን በማጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ ድርጅቶችን ዘርፈዋል" ብለዋል።

በምዕራብ አክቶቤ ከተማ በተቃዋሚዎች ላይ የአድማ መበተኛ ውሃ ጥቅም ላይ ውሏል። በአንዳንድ ቦታዎች የጸጥታ ኃይሎች ከተቃዋሚዎች ጋር መወገናቸውን የሚገልጹ መረጃዎችም እየወጡ ነው።

በመካከለኛው እስያ በምትገኘው ካዛኪስታን እየሆነ ስላለው ነገር ግልጽ የሆነ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚገልጹ መረጃዎችን ይፋ ቢያደርግም በተቃዋሚዎች ስለደረሰው የአካል ጉዳት እና ሞት ምንም አልተባለም። "በአገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ" መኖሩም ተገልጿል።

እሑድ የጀመረውን ተቃውሞ ለማስቆም መንግሥት ብዙ ሰዎች ለመኪናቸው የሚጠቀሙበት የጋዝ ዋጋ ጭማሪ እንዲቀር አድርጓል።

ከናዛርባይቭ ከኃላፊነት መነሳት በተጨማሪም ሁሉም የካቢኔ አባላት ከሥራ ለቀዋል።