ኮቪድ -19፡ ቻይና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በሁለተኛ ከተማዋ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

ዩዦ የተሰኘችው እና 1.1 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው የቻይና ከተማ ሦስት ምልክት የማያሳዩ ኮሮናቫይረስ የያዛቸው ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ትራንስፖርትን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአንድ ቀን ውስጥ ዘጋች።

ይህም ከታኅሳስ 13 ጀምሮ 13 ሚሊዮን ነዋሪ የያዘችውን ዢያን ላይ ከተወሰደው እርምጃ በኋላ ሁለተኛው ነው።

ይህ ጥብቅ እርምጃ የተወሰደው ቻይናዊያን በሰፊው ከሚያከብሩት አዲስ ዓመት እና በቤይጂንግ ከሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ከመካሄዱ በፊት ነው።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ወረርሽኑን አስመልክቶ "ቻይና ውጤታማ የመከላከያ ሥርዓት ዘርግታለች" ሲሉ ጨዋታው ሊጀመር አንድ ወር ሲቀረው ለጋዜጠኞች መናገራቸው ይታወሳል።

ቃል አቀባዩ ከገለጿቸው ሥርዓቶች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች ወደ ኦሎምፒክ መንደሩ መግባት የጀመሩ ሲሆን ይህም የቫይረሱን ሥርጭት ለመገደብ ከውጭው ዓለም ጋር ምንም ዓይነት አካላዊ ግንኙነት ሳይኖራቸው እንደሚቆዩ ተነግሯል።

በተመሳሳይም ተሳታፊዎች ብሎም ለጨዋታው ሽፋን ለመስጠት የሚመጡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቻይና ሲደርሱ ወደ ኦሎምፒክ መንደሩ በመግባት ጨዋታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንደሚቆዩ ታውቋል።

ከቤጂንግ በስተደቡብ ምዕራብ 700 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ዩዦ ባለሥልጣናት እንዳሉት ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ውስጥ መግታትና መቅረፍ ዜጎችም ሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ቅድሚያ የሚሰጡት ፖለቲካዊ ተግባር ነው።

የከተማዋ ነዋሪዎች በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ የተነገራቸው ሲሆን በሽታውን በመቆጣጠር ሥራ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ብቻ እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል።

ተመሳሳይ ፖሊሲ በምዕራባዊ ቻይና በምትገኘው የዢያን ከተማ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ያህል ሲተገበር ቆይቷል።

ባሳለፍነው ሰኞም ከተማው 95 የቫይረሱን ምልክት ያሳዩ ሰዎች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን ሥርጭቱ በጨመረበት ወቅት ከ150 በላይ ሰዎች በቀን ሲያዙ ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መቀነስ አሳይቷል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ይሁን እንጂ የከተሞቹ መዘጋት የቫይረሱን ሥርጭት የሚቀንስ ቢመስልም ሌሎች ጥያቄዎችን አስከትሏል። የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች እንደሚያሳዩት ነዋሪዎች በምግብ እጦት ስጋት ውስጥ በመግባታቸው እቃዎቻቸውን ለመሸጥ ተገደዋል።

ዋንግ የተባለ ነዋሪ ራዲዮ ፍሪ ኤዥያ ለተሰኘ አንድ ሚዲያ እንደተናገረው "ሰዎች በተመሳሳይ ሕንፃ ውስጥ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር እቃዎችን እየተለዋወጡ ነው፤ ምክንያቱም ከአሁን በኋላ የሚበሉት በቂ ምግብ ስለሌላቸው" ሲል ተናግሯል።

የዜና ማሰራጫው አንድ ግለሰብ ዘመናዊ ስልክ እና ታብሌቱን በሩዝ ለመቀየር መሞከሩን ዘግቧል።