ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንቅስቃሴ በተገደበባት የቻይናዋ ከተማ የምግብ እጥረት ማጋጠሙ
በቻይናዋ ዢያን ከተማ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንቅስቃሴ መገደቡን ተከትሎ ነዋሪዎች በቂ ምግብ እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው።
ሆኖም ባለስልጣናቱ በበቂ ሁኔታ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት አለ እያሉ ነው።
ባለሥልጣናቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ከ13 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሉባት የዢያን ከተማ የእንቅስቃሴ ገደብና በቤታቸው እንዲቆዩ ታዝዘዋል።
ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ካሉ ሌሎች የእንቅስቃሴ ገደቦች ጋር ሲነፃፀር የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብ መሸመት ለመሳሰሉ አስፈላጊ ጉዳዮች እንኳን መንቀሳቀስ ተገድበዋል።
መንግሥት መሰረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶችን ቢያቀርብም ነገር ግን ነዋሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እስካሁን እንዳልደረሳቸውና እና ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆኑም እየተናገሩ ነው።
በሰሜናዊቷ ዢያን ከተማ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል። በከተማዋ የተከሰተው ወረርሽኝ ቻይና በዜሮ ኮቪድ መርሃ ግብሯ ውስጥ የታየው ከፍተኛው ነው ተብሏል።
መጀመሪያ ላይ የተጣለው እገዳ በእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ሰው በየሁለት ቀኑ አንድ ጊዜ ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ቁሳቁሶችን ለመግዛት እንዲወጡ ፈቅዶ ነበር።
ነገር ግን መመሪያው በያዝነው ሰኞ እንዲጠብቅ የተደረገ ሲሆን ለኮቪድ-19 ምርመራ ካልሆነ በስተቀር ነዋሪዎች የትም ቦታ እንዳይወጡ ከልክሏል።
ባለፉት ቀናት ነዋሪዎች ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶችን ለማግኘት እርዳታ ጥየቃ በዌይቦ ማህበራዊ ሚዲያ ጥሪ አድርገዋል። ብዙዎች እስካሁን ከመንግሥት መሰረታዊ አቅርቦት እንዳላገኙም ገልጸዋል።
"ሌሎች ግዛቶች ቀስ በቀስ መሰረታዊ ሸቀጦች እያገኙ እንደሆነ ሰምቻለሁ። ነገር ግን ምንም አላገኘሁም። ከግቢያችን ወደ ውጭ እንዳንወጣ ተከልክለናል። ከአራት ቀናት በፊት አንዳንድ ሸቀጦችን በኢንተርኔት ባዝም እስካሁን የደረሰኝ ነገር የለም። ለቀናት አትክልት ማግኘት አልቻልኩም" በማለት አንድ ግለሰብ በዌይቦ ላይ ጽፏል።
ሌላኛው ግለሰብ ደግሞ "የስርጭት ስራው በእኩል እየተሰራ አይደለም። እኔ ያለሁበት ወረዳ ምንም ያገኘው ነገር የለም። በቡድን ተቀናጁና እዘዙ ተብለን የነበረ ቢሆንም ዋጋው በጣም ውድ ነው" ብሏል።
በዚህ ሳምንት በኢንተርኔት ሲሰራጭ የነበረ አንድ ቪዲዮ በዢያን ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች በምግብ እጦት ከፖሊስ ጋር የጦፈ ክርክር ሲያደርጉ ያሳያል።
አንድ ግለሰብ ቤተሰቦቹ ያላቸው ምግብ እንዳለቀ ለባለስልጣናቱ ሲናገር የሚሰማ ሲሆን አንዲት ሴት "ለ13 ቀናት ያህል ተቆልፎብናል። የነዋሪዎችን መሰረታዊ ኑሮ ማስቀጠል አልተቻለም። አትክልት ለመግዛት ከሶስት እስከ አራት ሰዓት ተሰልፈናል። ግን መሸጥ እንደማይቻል ተነገረን" ብላለች።
መንግሥታዊው ጋዜጣ ግሎባል ታይምስ እንደዘገበው በአንዳንድ ቦታዎች ምግብ ወደ መኖሪያ ግቢዎች ደጃፎች ይደርስ ነበር ነገር ግን ሸቀጦቹን ወደ ነዋሪዎች ደጃፍ የሚያደርሱ በቂ በጎ ፈቃደኞች አልነበሩም።
በርካታ አሽከርካሪዎች እራሳቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ በመሆናቸው በከተማዋ ሁሉ የአቅርቦት እጥረት ነበር።
ባለሥልጣናቱ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ እለት "የሰራተኞች ቁጥር መቀነስ ፣ ከሎጅስቲክስ እና ከስርጭት ችግሮች ጋር በተያያዘ" ለከተማው አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለማቅረብ እክል እንደተፈጠረ አምነዋል ።
ሆኖም ሐሙስ ዕለት የሀገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የዢያን ነዋሪዎች አስፈላጊ አቅርቦቶች በበቂ መልኩ እያገኙ እንደሆነ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የመንግሥት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በበኩላቸው በሃዝማት ሱት ውስጥ ያሉ ሰራተኞች እንደ እንቁላል፣ ስጋ እና አትክልት የመሳሰሉ አስፈላጊ ምግቦችን በፕላስቲክ ከረጢቶች አሽገው ቤት ለቤት ሲያደርሱ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን አውጥተዋል።
ቻይና ጥብቅ የተባለውን የዜሮ-ኮቪድ መርሃ ግብሯን ማስተዋወቋን ተከትሎ በዢያን ከተማ የአውቶቡስ ጣቢያዎች ተዘግተዋል፣ ወደ ውጪ የሚደረጉ በረራዎች ተሰርዘዋል እንዲሁም ከተማዋ በምትገኝበት የሻንሲ አውራጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኮቪድ-ምርመራዎችን አድርጋለች።
ዢያን ከታህሳስ ጀምሮ ከ1ሺህ 300 በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ነዋሪዎችን መዝግባለች።
በቅርብ ጊዜ ያገረሸው ወረርሽኝ ቻይና በየካቲት ወር 2022 የክረምት ኦሎምፒክን ለማስተናገድ ሽር ጉድ በምትልበት ወቅት የዜሮ-ኮቪድ መርሃ ግብሯን ለማስጠበቅ እያደረገችው ያለችውን እርምጃ ጥርጣሬ ውስጥ ጥሎታል።
ቻይና ኮቪድ- 19ን ለአለም አቀፍ የስፖርት ዝግጅቶች "ትልቁ ስጋት" ስትል ጠርታዋለች።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበባት ቻይና በአሁኑ ወቅት ከ 131 ሺህ 300 በላይ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የሚገኙባት ሲሆን 5 ሺህ699 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት የቅርብ ጊዜ መረጃ ያሳያል ።