ኦሚክሮን፡ በደቡብ አፍሪካ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨመረ

የደቡብ አፍሪካ ጤና ኃላፊዎች ኦሚክሮን የሚል ስያሜ በተሰጠው ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ኮሮናቫይረስ የሚገኘባቸው ሰዎች በእጥፍ ከፍ ብሏል አሉ።

በደቡብ አፍሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 8ሺህ 500 የተጠጋ ሲሆን፤ ከዛ ቀደም ባለው ቀን ተመዝግቦ የነበረው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4ሺህ 300 የሚጠጋ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት ቢያንስ በ24 አገራት አዲሱ ኦሚክሮን የኮሮናቫይረስ ዝርያ መገኘቱን አስታውቋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ በቅርቡ ይህ ቫይረስ የተገኘባቸው አገራት ናቸው። ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን እና ቤልጂየም እንዲሁ ኦሚክሮን ከተገኘባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ይህን ቫይረስ ቀድማ ሪፖርት ያደረገችው ደቡብ አፍሪካ ነበረች። የአገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት ካለፈው የፈረንጆቹ ወር ወዲህ በምርመራ ካረጋገጣቸው የኮሮናቫይረስ ኬዞች መካከል ኦሚክሮን የ70 በመቶ ድርሻ እንዳላው አስታውቋል።

በዚህ ቫይረስ ተይዘው ወደ ሆስፒታል ከመጡት መካከል አብዛኛዎቹ የኮቪድ-19 ክትባት ያልወሰዱ መሆናቸውን ተቋሙ አስታውቋል።

በደቡብ አፍሪካ የክትባት እጥረት ባለመኖሩ ደቡብ አፍሪካውያን ክትባት እንዲወስዱ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ እያሳሰቡ ነው።

እስካሁን ድረስ ኦሚክሮንን በተመለከተ ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ተብለው የሚሰጡ ክትባቶች ይህን ዝርያ መቋቋም ስለመቻላቸው የሚታወቅ ነገር የለም።

የዓለም ጤና ድርጅት ኦሚክሮን የመዛመት እድሉ ከፍተኛ ነው በማለት "አሳሳቢ ዝርያ" ሲል ፈርጆታል።

የዚህ ቫይረስ መገኘትን ተከትሎ በርካታ አገራት ከደቡብ አፍሪካ አገራት የሚደረጉ በረራዎች ላይ እገዳ ጥለዋል።

በዚህ የጉዞ እግዳ ሰለባ ከሆነችው አንዷ ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፤ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደቡብ አፍሪካ ቫይረሱን በማግኘቷ ልትደነቅ እንጂ ልትቀጣ አይገባም በማለት የጉዞ እገዳውን ተቃውመዋል።

በተመሳሳይ ፕሬዝደንት ራማፎስ የጉዞ እግዱን ተቃውመዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፤ በጉዞ ክልከላዎቹ የደቡብ አፍሪካ አገራት እየተቀጡ ነው ብለዋል።